አቶ አህመድ ሺዴ ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ

መጋቢት 16/2013 (ዋልታ) – የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በብራስልስ ተወያዩ።

ከኮሚሽኑ ዓለምአቀፍ ትብብር ኮሚሽነር እና ከቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ጋር የተወያዩት የገንዘብ ሚኒስትሩ፣ ስለሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ፣ እየተካሄደ ስላለው ልማትና ለመጪው ምርጫ እየተደረገ ስላለው ዝግጅት ገለፃ አድርገዋል።

በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረስ እየተደረገ ስላለው ጥረትና የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ካሉ ለማጣራት እየተሰራ ስላለው ስራም አብራርተዋል፡፡

አቶ አህመድ ሺዴ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ስላለው ሁኔታና የህዳሴ ግድብ ድርድርን አስመልክቶም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በበኩላቸው፣ በምስራቅ አፍሪካ ሁነኛ ስትራቴጂክ አጋሩ ለሆነችው ኢትዮጵያ ትልቅ ዋጋ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

የኮሚሽኑ የስራ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ ልማቶችን በመልካም ጎን  እንደሚመለከቷቸው አስታውቀዋል፡፡

በትግራይ ክልል የተፈፀሙ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች ካሉ በአግባቡ አጣርቶ ፍትህ እንዲሰፍን ማድረግ እንደሚገባም ኃላፊዎቹ አንስተዋል፡፡

ሁለቱ ወገኖች እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ2016 የተደረሰውን የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት ይበልጥ ተግባራዊ ለማድረግ ተስማምተው እየሰሩ መሆናቸውን ከብራስልስ የኢትዮጵያ ኢምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡