አቶ አገኘሁ ተሻገር ከዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ተወካይ ጋር እየተወያዩ ነው

ነሐሴ 25/2013 (ዋልታ) – የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር ዩኒሴፍ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው በቻግኒ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የነበሩ ወገኖችን በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ርእሰ መስተዳድሩ አሸባሪው እና ወራሪው የትህነግ ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች በከፈተው ጦርነት በርካታ ዜጎች መገደላቸውን እና በርካቶች መፈናቀላቸውን ገለፃ አድርገውላቸዋል።
አሸባሪው ቡድን በፈጸመው ወረራ ሕፃናት፣ ሴቶች እና አረጋዊያን የከፋ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን እና በርካታ የትምህርት እና የጤና መሠረተ ልማቶች መዘረፋቸውንም አብራርተዋል።
በዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ተወካይ አዴል ክኾድር በአፋር እና አማራ ክልሎች ተፈናቃዮችን ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን ገልጸው፣ ዩኒሴፍ ለተፈናቃዮች አፋጣኝ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ እንደሚሠራ አስረድተዋል።
ከውይይቱ በኋላም አዴል ክኾደር የተለያዩ የህክምና እና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስን ድጋፍ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል የዘገበው አሚኮ ነው።