አቶ ደመቀ መኮንን በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ጀፈሪ ፈልትማን ጋር ተወያዩ

ግንቦት 03/2013 (ዋልታ) – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ከሆኑት አምባሳደር ጀፈሪ ፈልትማን ጋር ተወያዩ፡፡

ውይይታቸውም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር፣ በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ፣ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታዎች እንዲሁም በመጪው 6ኛው ብሔራዊ ምርጫን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጿል።

በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔዎች በተለይም በትግራይ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትንና መልሶ ማቋቋም ረገድ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር አካሄድን በተመለከተ፣ መጪው ብሔራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲካሄድ ስለተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች በተመለከተ ለልዩ ልዑኩ አስረድተዋቸዋል።

የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ በድርድር እልባት እንዲያገኝ በኢትዮጵያ በኩል ያለው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑንም አቶ ደመቀ መኮንን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነትን በማንሳት፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል በተለያዩ ዘርፎች ያለውን ትብብር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

አምባሳደር ጀፈሪ ፈልትማን በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን ጠቅሰው፣ በሰላምና መረጋጋት ጉዳዮች በትብብር ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።

አያይዘውም የታላቁ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በማስቀጠል በሁሉም ተደራዳሪ አካላት ዘንድ ተቀባይነት ያለው መፍትሔ ላይ ለመድረስ በሚደረገው ጥረት በሀገራቸው በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።