ሰኔ 25/2013 (ዋልታ) – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አኒ ሊንድ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በስልክ ተወያዩ።
በውይይቱ አቶ ደመቀ ኢትዮጵያና ስዊድን ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ግንኙነት ያላቸው ወዳጅ አገራት መሆናቸውን ጠቅሰው በሁለቱ ሀገራት መካከል የቆየውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሰብዓዊነት በማስቀደም በትግራይ ክልል የሚከሰተውን የሰብዊነት ቀውስና የኢኮኖሚ ውድመትን ለማስቀረት የተናጥል ተኩስ አቁም ማወጁን አስረድተዋል፡፡
የህወሃት ሽብር ቡድን በተመሳሳይ ከጠብ አጫሪነት በመታቀብ ግጭት እንዲያቆምና ለክልሉ አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር መተባበር እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
ለክልሉ የሰብአዊ ዕርዳታ ተደራሽ እንዲሆን የኢትዮጵያ መንግሰት ከረድኤት ድርጅቶች ጋር ተባብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን የገለጹት አቶ ደመቀ÷ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
አኒ ሊንድ በበኩላቸው መንግስት በትግራይ ክልል የተናጠል ተኩስ አቁም እርምጃ መውሰዱን አድንቀዋል፡፡
በቀጣይም በክልሉ የሰብአዊ ዕርዳታ ተደራሽ እንዲሆን እና በክልሉ የተፈጠረው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በሚመለከተው አካላት በማጣራት እርምጃ እንዲወሰድ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለውን የድንበር ውዝግብ እና የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ሚኒስትሯ ላነሱት ጥያቄ÷ የኢትዮ-ሱዳን ድንበርን በተመለከተ ሱዳን ከያዘቻቸው ቦታዎች ለቃ እንዲትወጣ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ግፊት እንዲያደርግ ጥሪ እየተደረገ መሆኑን ተገልጾላቸል፡፡
አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ መንግሰት ከሱድን ጋር ጉዳዩን ለመፍታት በተቀመጡ አሰራሮች መሰረት ሰላማዊ መፍትሔ እንዲገኝ ፍላጎት መሆኑን አቶ ደመቀ አብራርተዋል፡፡
የህዳሴ ግድብን ድርድርን በተመለከተ የሱዳንና ግብፅ ወገን አለም አቀፋዊና ፖለቲካዊ በማድረግ ለተባበሩት መንግስታት የሚወስዱት አካሄድ አግባብነት እንደሌለው መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ መፍትሔ እንዲሰጠው በውሃ ሙሌት በተመለከተ በየምዕራፎች ድርድር እንዲደረግ የኢትዮጵያ አቋም መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሚኒስትሯም የህዳሴ ግድብ በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት መፍትሔ እንዲሰጠው የሚደግፉ መሆኑን በመጠቆም የስዊድን መንግሰት በኢትዮጵያ እየተካሄዴ ያሉ የለውጥ ስራዎችን ለመደገፍ እና ሌሎች ትብብሮች አጠናክሮ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡