የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሞሐመድ አብዲራዛቅን በቢሮአቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ኢትዮጵና ሶማሊያ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው፣ በህዝቦች መካከልም ጠንካራ ትስስር ያላቸው ጎረቤታሞች አገሮች መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ደመቀ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ኢትዮጵያ የሚቻለውን ሁሉ እንደሚታደርግ ቃል ገብተዋል።
በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ፣ በኢትዮጵያ ሊደረግ በታቀደው ብሔራዊ ምርጫ እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጓል።
ኢትዮጵያ ለሚታካሂደው ምርጫ ዝግጅት መጀመሯን የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተመሳሳይ ምርጫ ለሚታደርገው ሶማሊያም የተሳካ ምርጫ እንዲሆን ተመኝተዋል።
የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት የውጭ ጉዳይና ዓለምአቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሞሐመድ አብዲራዛቅ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ለአገራቸው መረጋጋት ሲታደርግ ለቆየችው አስተዋጽኦ አመስግነዋል።
አገራቸው ሶማሊያ በቅርብ ጊዜ ለሚታደርገው ምርጫ ከክልል መግሥታት ጋር በንግግር ላይ እንደምትገኝ ገልፀዋል።
አያይዘውም አገራቸው በሰሜን ኢትዮጵያ አጋጥሞ የነበረው ጉዳይ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ መሆኑን እንደምትረዳና ለዚህም ኢትዮጵያ የህግ የበላይነት ለማስከበር ያደረገችውን ዘመቻ እንደምትደግፍ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ አያይዘውም ሁለቱ አገሮች በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ትብብር እንዲጠናከር በጋራ ለሚያደርጉት ጥረት አገራቸው ቁርጠኛ መሆኗን መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡