አቶ ደመቀ መኮንን ከተመድ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የምሥራቅ አፍሪካ ተጠሪ ጋር ተወያዩ

አቶ ደመቀ መኮንን

ሚያዝያ 20/2013 (ዋልታ) – የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የምሥራቅ አፍሪካ ተጠሪ ሚስተር ማርሴል አክፖቮን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

አቶ ደመቀ በወቅቱ ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ረገድ በምታከናውናቸው ተግባራት ድርጅቱ ለሚሰጠው ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸው፣ ይኸው መልካም ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተም የተመድ የከፍተኛው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በጋራ ምርመራ ለማካሄድ መወሰኑን ኢትዮጵያ በአድናቆት የምትመለከተው መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በዜጎቹ ላይ የሚከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከማንኛውም አካል በላይ ኃላፊነት የሚሰማው መሆኑን ጠቅሰው፣ የምርመራው ውጤትን ተቀብሎ የድርጊቱ ፈፃሚዎችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ያለውን ዝግጁነትንም አረጋግጠዋል።

የተለያዩ አካላት ባልተረጋገጠ መረጃ በመመሥረት በመንግሥት ላይ ገንቢ ያልሆኑ  ትችቶችን  እየተሰነዘሩ መሆኑን ያወሱት አቶ ደመቀ፣ የምርመራው ውጤት በመሬት ያለውን ተጨባጭ እውነታ እንደሚያሳይ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሚያከናውናቸው ተግባራት ከበሬታ ያተረፈ ተቋም መሆኑን ገልጸው፣ ተቋሙ በማይካድራ እና አክሱም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ያከናወናቸውን የምርመራ ተግባራት በአብነት አንስተዋል።

አቶ ደመቀ በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ፣ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ሁኔታን እንዲሁም የታላቁ የኢትዮጵያ የሦስትዮሽ የድርድር ሂደትን በተመለከተም ለተጠሪው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የተመድ ከፍተኛው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የምሥራቅ አፍሪካ ተጠሪ ሚስተር ማርሴል አክፖቮን በበኩላቸው፣ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በሚያደርጉት የሥራ እንቅስቃሴ በኢትዮጵየሰ በኩል እየተደረገላቸው ለሚገኘው ትብብር እና ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ድርጅታቸው ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በትግራይ የጋራ ምርመራ ማካሄድን ጨምሮ  በሌሌችም ተዛማጅ ሥራዎች መልካም የሥራ ግንኙነት መኖሩን ጠቅሰው፣ ይህም ለሥራቸው  ስኬት አዎንታዊ  አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በዘርፉ ዓለም አቀፍ ግዴታዋን ለመወጣት በምታደርገው ጥረት ድርጅታቸው ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

ሚስተር ማሪሴል አክፖቮ ሥራቸውን ለመወጣት በሚያደርጉት እንቅስቀሴ በኢትዮጵያ በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አቶ ደመቀ ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።