አቶ ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ዕርዳታ ሃላፊ ጋር ተወያዩ

ሐምሌ 23/2013 (ዋልታ) – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች እና አስቸኳይ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ከሆኑት ማርቲን ግሪፍትስ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ኃላፊው በትግራይ ክልል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ፣ የሰብአዊ ድጋፍ ሥራዎችን ለመገምገም እንዲሁም በትግራይ እና አማራ ክልል የስራ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል፡፡

በውይይቱ ድርጅቱ እ.ኤ.አ.ከ1984 ጀምሮ በኢትዮጵያ የሰብአዊ ድጋፍ በማድረግ፤ የአደጋ ጊዜ ዝግጁነትና ምላሽ  አቅም እንዲጎለብት ላደረገው ውጤታማ ሥራ  አቶ ደመቀ  ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ይሁን አንጂ በትግራይ ክልል ከተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ በዋና መስሪያ ቤቱ  ደረጃም ሆነ በሀገሪ ውስጥ ወኪል ጽህፈት ቤት በኩል በሚፈለገው ደረጃ ድጋፍ አለማድረጉን  ጠቁመዋል፡፡

በትግራይ ክልል ካለው ሁኔታ ጋር ተያይዞ ታዓማኝነት የሌላቸውን  መግለጫዎችንና ሪፖርቶችን በማቅረብ ድርጅታቸው ለተጫወተው አሉታዊ ድርጊት የኢትዮጵያን መንግስት ያሳዘነ መሆኑንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም እርምጃ ቢወስድም ከዚህ በተቃራኒ  የህወሃት ቡድን  የጥፋት  እና የግጭት  መንገድን  በመከተል ህጻናትናን ጭምር ለጦርነት በመመልመል ተግባር መሳተፉን ለሥራ ኃላፊው ተገልጿል፡፡

አቶ ደመቀ በህወሃት ጠባ ጫርነት ምክንያት ምግብ እና ምግብ -ነክ ዕርዳታ የጫኑ 170 ተሽከርካሪች ወደ ትግራይ የሰብአዊ ድጋፍ እንዳያጓጉዙ ለሳምንታት በሰመራ መታገታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ እንዳመላከተው በዚህ ሳምንት ዕሮብ 40 የሚሆኑ ተሽከርካሪች ወደ መቀሌ ጉዞ የጀመሩ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን ተገልጿል፡፡

ህወሃት የግጭት መንገድ እየተከተለ፣ ህጻናትን ለጦርነት እያሰለፈ በመሆኑ እንዲሁም የሰብአዊ ዕርደታ ተደራሽነት በማወኩ ቡድኑ ለችግሮቹ  ሃላፊነት እንዲወስድና ተጠያቂ እንዲሆን ተቋማቸው እርምጃ እንዲወስድ አቶ ደመቀ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ኃላፊው በበኩላቸው ተቋማቸው ለሚያከናውነው ሥራ ስለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው፤ በቀጣይ ከመንግሰት ጋር በመቀራረብ እና በመወያየት ለመሥራት ዝግጁ መሆኖቸውን አስረድተዋል፡፡

በትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት እየቀነሰ መሄዱን በማንሳት ዕርዳታ ተደራሽ ይሆን ዘንድ አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር የስራ ኃላፊው  ትብብር ጠይቀዋል፡፡

መንግስት የሰብአዊ ዕርደታ ለክልሉ ተደራሽ እንዲሆን የሚችለውን ጥረት እንደሚያደር አቶ ደመቀ አረጋግጠዋል፡፡