የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ህብረት አምባሳደሮችና ከሀገራቱ ተወካዮች ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ፡፡
አቶ ደመቀ በውይይቱ ወቅት በትግራይ ክልል መንግስት እና የዕርዳታ ድርጅቶች እያካሄዱት ስለሚገኘው ሰብዓዊ ጥረት አብራርተዋል፡፡
መንግስት መድሃኒቶችን ጨምሮ ምግብ እና ምግብ ነክ ድጋፎችን በተለያዩ 92 ማሰራጫ ጣቢያዎች ማዳረሱን እንዲሁም በክልሉ እየቀረበ በሚገኘው የሰብዓዊ ድጋፍ የመንግስት ተቋማት ዓለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች እና የዕርዳታ ድርጅቶች በትብብር እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡
ከመልሶ ግንባታው በተጨማሪ የተቋረጡ የባንክ፣ መብራት እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች ወደ ስራ እየገቡ መሆኑንም አቶ ደመቀ አስረድተዋል፡፡
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርም ከፌደራል መንግስት ጋር በመቀናጀት በሁሉም አካባቢዎች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
በክልሉ እየተነሱ የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክሶችን በተመለከተ መንግስት ጉዳዩን ለማጣራት ያለውን ቁርጠኝነት የገለጹት አቶ ደመቀ፣ በውይይታቸው ከትግራይ ክልል ኢትዮጵያ በቅርቡ ስለምታከሄደው ጠቅላላ ምርጫ ለአምባሳደሮቹ አብራርተዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት አምባሳደሮችና የሀገራቱ ተወካዮች በበኩላቸው፣ አሳሳቢ ነው ባሉት ጉዳይ ላይ ገለጻ ስለተደረገላቸው አቶ ደመቀን አመስግነዋል፡፡
ውይይቱ ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት በቅርበትና በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡