አቶ ደመቀ መኮንን ከዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ጋር ተወያዩ

አቶ ደመቀ መኮንን

ሚያዝያ 09/2013 (ዋልታ) – የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) የኢትዮጵያ ተወካይ ማውሪን አቼንጌ ጋር ተወያይተዋል።

አቶ ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ ህገወጥ ስደትን ለመከላከልና በህገወጥ ስደት ሳቢያ እንግልት የሚደርስባቸውን ዜጎች ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ እያደረገች ያለውን ጥረት በተመለከተ ማብራርያ ሰጥተዋል።

በዚህ ተግባርም ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት ሁነኛ አጋር እንደሆነም ተናግረዋል።

አቶ ደመቀ አክለውም መንግስት ህገወጥ ስደትን ከመሰረቱ ለማስቀረት በርካታ ተግባራትን እየሰራ እንደሆነም አብራርተዋል።

የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ማውሪን አቼንጌ በበኩላቸው፣ ተቋማቸው ኢትዮጵያ ህገወጥ ስደትን ለማስቆም የምታከናውነውን ተግባር መደገፉን አሁንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ስደተኞችን ፍላጎቶች ለመፍታት ከኮቪ-19 ጋር ተያይዘው ከሚነሱ ተግዳሮቶች አንፃር ከኢትዮጵያ መንግስት እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀራርቦ መስራቱን ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ እንደ አይ.ኦ.ኤም. ባሉ አግባብነት ባላቸው ተቋማትና ባለድርሻ አካላት መካከል የስደተኞችን መብትና ፍላጎት ለማስጠበቅ የሚደረግ ትብብር ወሳኝ ነው ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡