አቶ ደመቀ መኮንን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት

ሐምሌ 12/2013 (ዋልታ) – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሊት መርሃግብር በተሳካ ሁኔታ በመከናወኑ እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን አብሮ ደስ አለን ያሉት አቶ ደመቀ፣ በቀጣይ የሃገሪቱን የመልማት ፍላጎት ጥያቄን በሚመልስ መልኩ የጀመርነው ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ በህዝባችን የነቃ ተሳትፎ እና ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ተፈጥሮ የሰጠችንን ታላቅ ፀጋ አልምተን ለመጠቀም በገንዘባችሁ፣ በጉልበታችሁ፣ በላባችሁና በዕውቀታችሁ ባደረጋችሁት ብርቱ ርብርብ ለዚህ ታሪካዊ ስኬት በመብቃታችን እንኳን ደስ አለን ሲሉም አክለዋል።

በዚህ የስኬት ግለት ሃገሪቱን ለውጪ አካላት ተጋላጭ የሚያደርጉ ሃይሎችን በተባበረ ክንድ መመከትና ሴራቸውን ማምከን እንደሚገባም አሳስበዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ታሪካዊ ፕሮጀክት በዚህ የስኬት ደረጃ ያደረሰ እንዲሁም በብዙ ጫናዎች ሳይበገር ሰላማዊ ምርጫ ያካሄደ ህዝብ አንድነቱን አጥብቆና ጠብቆ ሲተም ለውጤት እንደሚበቃ ትልቅ ማሳያ መሆኑን መመልከት ይቻላል ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክታቸው ኢትዮጵያን በየትኛውም አቅጣጫ የሚዳፈሩ እና የውጪ አካላት ፍላጎት አስፈፃሚ የሆኑ ሃይሎች ዳግም እንዳይመለሱ ህዝቡ ተባብሮ ሃያልነቱን ማረጋገጥ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ባለፉት ጊዜያት ከውስጥ እና ከውጭ በርካታ ሃይሎች የፈጠሩብንን ጫናዎች በጥበብ መሻገራችን አይዘነጋም፤ ወደፊትም ለሚጠብቁን ፈተናዎችም ህዝቡ ህብረቱን አጠናክሮ በንቃት መመከት ይጠበቅበታል ነው ያሉት።

ለዚህ ታሪካዊ ምዕራፍ በመድረሳችን በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ ያሉት አቶ ደመቀ፣ በዘላቂነት አንድነታችንን አጠናክረን ትውልድ እና ሃገርን በድል እንድናሻግር ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል።