የካቲት 18/ 2013 (ዋልታ) – አውስትራሊያ ጎግል እና ፌስቡክ በአገሯ የዜና ይዘቶችን ሲያሰራጩ ክፍያ እንዲከፍሉ የሚያደርግ በአለም አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያውን ሕግ አፀደቀች፡፡
ይሁንና ሁለቱ ግዙፍ የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የፀደቀውን አዲሱን ህግ ክፉኛ ተቃውመዋል ነው የተባለው፡፡
ባለፈው ሳምንት በአዲሱ ህግ እሰጣገባ ሳቢያ ፌስቡክ ሁሉንም የዜናዎቹን ይዘቶች በአገረ አውስትራሊያ እገዳ ጥሎ የነበረ ቢሆንም በዚህ ሳምንት ግን ኩባንያው ከአገሪቱ መንግስት ጋር ባደረገው ድርድር ውሳኔውን መቀልበሱን ነው የተነገረው፡፡
ሁለቱ ኩባንያዎች የአውስትራሊያ መንግስት ሕጉን እንዲያሻሽል የማግባባት ስራ እየሰሩ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
ፌስቡክና ጉግል እያንዳንዳቸው በሚቀጥሉት 3 ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚዲያ እንዱስትሪ 1 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ለማድረግ እቅድ እንዳላቸው መግለጻቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡