አየር መንገዱ ‘ሳብሬ’ ከተሰኘ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጋር አብሮ ለመስራት ተስማማ

ጥቅምት 02/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ “ሳብሬ” ከተሰኘ የሶፍትዌርና የቴክኖሎጂ አቅራቢ ኩባንያ ጋር ለመጪው ሰባት ዓመታት አብሮ መሥራት የሚያስችለውን የ110 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ሥምምነት አደሰ።

በሥምምነቱም መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ “ሳብሬ-ሶኒክ” የተሰኘውን የሳብሬ የመንገደኞች አገልግሎት ሥርዓት ቴክኖሎጂ መጠቀሙን ይቀጥላል ተብሏል።

ይህም አየር መንገዱ የሽያጭና የአገልግሎት ሥርዓትን ለማዘመን፣ የገቢ መጠኑን  ለመጨመርና ለመንገደኞችም ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።

ከዚህ በተጨማሪም የሳብሬ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት ለአየር መንገዱ ተሳፋሪዎች በመረጃ ላይ የተመረኮዘ ውሳኔ ለማሳለፍ እንደሚረዳም ኤር 101 በድረ-ገጹ አስነብቧል።

የሳብሬ ኮርፖሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ዲኖ ጌልመቲ እንዳሉት “የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጽዕኖ ውስጥ ሆኖም በአቬሽን ኢንዱስትሪው ስኬት ማስመዝገቡን ቀጥሏል” ብለዋል።

ከዚህ በተጓዳኝ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የአየር መንገዶችን ተወዳዳሪነትና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፍላጎትን እያቀላጠፈ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ግዙፉ የአፍሪካ የአቬዬሽን ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድም ተለዋዋጭ እየሆነ ከመጣው ዓለም ጋር እራሱን እያጣጣመ አገልገሎቱን  እያጠናከረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሥምምነቱም አየር መንገዱ በገበያ ፍላጎትና ውድድር ላይ የተመሠረተ የዋጋ እና አገልግሎት አሰጣጥ ምክረ ሃሳቦችን በማቅረብ ተወዳዳሪና ተጠቃሚነቱን ያሳድጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፤ “ጠንካራና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መኖሩ ለአየር መንገዱ የስኬት ታሪክ ቁልፍ ሚና ይጫወታል” ብለዋል።

የሳብሬ የደህንነት ቴክኖሎጂም አየር መንገዱ ከአዲሱ የዓለም ገጽታ ጋር በፍጥነት ለመላመድ እንደሚረዳው ገልጸዋል።