አየር መንገዱ አምስት ተጨማሪ የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖችን ሊገዛ ነው

የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ግንቦት 18/2014 (ዋልታ) በአፍሪካ ትልቁ እና ቀዳሚው የአቪዬሽን ግሩፕ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖቹን ቁጥር ለማሳደግ አምስት ተጨማሪ ቦይንግ 777 የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች ማዘዙን አስታውቋል።

አየር መንገዱ ለመግዛት ያዘዛቸው አምስቱ አውሮፕላኖች የቅርብ ጊዜ እና ዘመናዊ የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች መሆናቸውን ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው “እነዚህ አምስት የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች ከዚህ በፊት በነበሩት የካርጎ አውሮፕላኖች ላይ መጨመራቸው እያደገ የመጣውን የካርጎ አገልግሎት ፍላጎት ለማሟላት ያስችለናል” ብለዋል።

አዲሱ ትዕዛዝ አየር መንገዱ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ያለውን አጋርነት የበለጠ ከማጠናከር ባሻገር የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች መጠን ማደጉ የድርጅቱን የማጓጓዣ አገልግሎት አቅምን እና ቅልጥፍናን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያደርሰውም ተናግረዋል።

አየር መንገዱ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ማቅረብ በሚችለው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ደንበኞቹን ለማገልገል ሁልጊዜ የሚተጋ መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈፃሚው አመልክተዋል።

የቦይንግ የሽያጭ እና ግብይት ምክትል ፕሬዝዳንት ኢህሳን ሙኒር በበኩላቸው አየር መንገዱ የካርጎ አገልግሎቱን ለማሟላት በቦይንግ ላይ ለጣለው አመኔታ አመስግነው ተጨማሪ አውሮፕላኖቹ የአየር መንገዱን የቅርብ ጊዜ ፍላጎት የሚያማሉ እንደሆኑ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ሰዓት ዘጠኝ ቦይንግ 777 የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች ባለቤት ሲሆን አምስት ተጨማሪ አውሮፕላኖችን ያዘዘው የጭነት አገልግሎቱን ከፍ ለማድረግ መሆኑ ተገልጿል።

በአሁኑ ሰዓት በገበያው ላይ መሪ የሆነው ቦይንግ 777 የዕቃ ጫኝ አውሮፕላን የዓለማችን ግዙፉ እና ረጅም ርቀት መጓዝ የሚችል ባለሁለት ሞተር አውሮፕላን መሆኑን አየር መንገዱ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጿል።

ከቀድሞዎቹ ጋር ሲነፃፀርም በ17 በመቶ ያነሰ ነዳጅ የሚጠቀም እና አነስተኛ የበካይ ጋዝ ልቀትን መያዝ ይችላል ተብሏል።

 

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!