አየር መንገዱ አዲስ የቦርድ አባላትን ይፋ አደረገ

መጋቢት 15/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ የቦርድ አባላትን ይፋ አደረገ።

የቦርዱ ሰብሳቢ ግርማ ዋቄ አዳዲሶቹን የቦርድ አባላት ይፋ አድርገዋል።

በዚህም መሰረት ተክለ ወልድ አጥናፉ፣ ተመስገን ጥሩነህ፣ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ፣ ታደሰ ጥላሁን፣ ግርማ ዋቄ፣ ረታ መላኩ እንዲሁም አለማየሁ አስፋው የተባሉ ግለሰቦች የቦርድ አባል ሆነዋል፡፡

የቀድሞ ሥራ አስፈፃሚ ተወልደ ገብረ ማርያም በህመም ምክንያት በፈቃዳቸው ያስገቡትን መልቀቀያ አዲሱ ቦርድ ተቀብሎ ማጽደቁም ተነግሯል፡፡

አዲሱ ቦርድ ባደረገው ስብሰባ መስፍን ጣሰውን የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አድርጎ ሾሟል።

አዲሱ ተሿሚ በአሁኑ ጊዜ ቶጎ ባለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እህት ካምፓኒ አስካይ በሥራ አስፈፃሚነት ላይ የሚገኙ ሲሆን አዲሱን ሹመት መቀበላቸውም ተነግሯል።

ኃላፊነቱን መጥተው እስኪቀበሉም ቡሴራ አወል ተቋሙን በውክልና እየመሩ ይገኛሉም ተብሏል።

በትዕግሥት ዘላለም