አየር መንገዱ የሲኤንኤን ዘገባ ተቃወመ

መስከረም 28/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጦር መሳሪያና ሌሎች ያልተፈቀዱ እቃዎችን አጓጉዟል በሚል ሲ ኤን ኤን ያሰራጨዉ ውንጀላ መሰረተ ቢስ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ሲኤንኤን የዜና አውታር የኢትዮጵያ አየረ መንገድ የጦር መሳሪያዎችን እንዲሁም ሌሎች ያልተፈቀዱ እቃዎችን አጓጉዟል ሲል ትላንት ሀሰተኛ መረጃ በገጹ አስነብቧል፡፡
ይህንን ተከትሎ አየር መንገዱ ሲ ኤን ኤን ያሰራጨዉ ውንጀላ መሰረተ ቢስ መሆኑን በመጥቀስ በዘገባው ያካተታቸው እቃዎችን አየር መንገዱ አያቃቸውም ሲል በመግለጫው አስፍሯል፡፡
እቃዎች የሚጓጓዙት በአይ ኤ ቲኤን ደረጃዎች መሠረት ተፈትሸው እንዲሁም በብሔር ምክንያት የታገደ ወይም የተባረረ ሰራተኛ አለመኖሩን እና ይህንንም ከሰው ሀብት መዛግብት ሊረጋገጥ ይችላል ሲል ውንጀላውን ውድቅ አድርጓል፡፡
ለዚህም የተሳሳተ ውንጀላ ሚዲያዉ እርማት እንዲያደርግ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሳስቧል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁሉንም ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ተዛማጅ ደንቦችን እና መስፈርቶችን በጥብቅ የሚያከብር፣ በሁሉም የሥራ ክንውኖች ውስጥ የሲቪል አቪዬሽን ደንቦች ተከትሎ የሚሰራ፣ በማንኛውም የጦር መሣሪያ መጓጓዝ ውስጥ ተሰማርቶ የማያውቅ መሆኑን ለሁሉም ተሳፋሪዎቻችን እና ለህዝቡ እናረጋግጣለንም ብሏል፡፡