ጥር 1/2014 (ዋልታ) አዲሱ የመከላከያ ሚኒስቴር ዋና መስርያ ቤት ህንጻ ምረቃ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት እየተከናወነ ይገኛል፡፡
በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) አዲሱ የመከላከያ ሚኒስቴር ህንጻ ለቀጣይ ትውልድ ታስቦ የተሰራና ደማቅ አሻራ ያረፈበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን በርካታ የጦር ውጊያዎችን ያሳለፍንና በመስዋትነትም ነፃነታችንን በማስጠበቅ አኩሪ ታሪክ የፃፍን ህዝቦችን ነን ያሉት ሚኒስትሩ የዛሬው ትውልድም ይህን ልምምድ የሚደግምበት የታሪክ አውድ ውስጥ እንደሚገኝ ማስተዋል ይገባዋል ብለዋል፡፡
በዛሬው ዕለት በይፋ የተመረቀው የጠቅላይ እዝና የመከላከያ ዋና መስሪያ ቤት ህንጻ ደረጃውን ከጠበቀ የግንባታ ስራ በዘለለ አጠቃላይ የዙሪያ ገብ የመከላከያ ግንባታ ስራ የሚንጸባረቅበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዙሪያ ገብ የሰራዊት ግንባታ በህገመንግስቱ እና በብሄራዊ መግባባት በተደገፉ ገዥ የሕግ ማዕቀፎች እንደሚመሰረት የገለፁት የመከላከያ ሚኒስትሩ ይህም የኢትዮጵያን ኅልውናና ሉአላዊነት የሚያረጋግጥና የሚያስጠብቅ፣ የማይነቃነቅ ፅኑ ዘብ የሆነ ኃይል መገንባትን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ዛሬ የተመረቀው ህንፃ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ የያዘ፣ የስማርት ህንጻ ፅንሰ ሃሳብን ያሟላ፣ የመሬት መንቀጥቀጥን መከላከል የሚችል መሆኑን የተናገሩት የመከላከያ ሚኒስትሩ ለቀጣይ ትውልድ ታስቦ የተሰራና ደማቅ አሻራ ያረፈበት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ኢብኮ እንደዘገበው በህንጻ ግንባታው ላይ የቅርብ አመራር በመስጠትና ልዩ ክትትል በማድረግ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሚና ትልቅ እንደነበረም ተናግረዋል፡፡