አዲሱ የእንግሊዝ የሌበር መንግስት አፍሪካ ላይ የሚከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ

የሌበር ፓርቲ በስልጣን ላይ የነበረው በጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር አገዛዝ ዘመን ነበር። በዘንድሮው የእንግሊዝ ምርጫ ከ14 ዓመት በኋላ ወደ ስልጣን የተመለሱት ሌበር ፓርቲ ዓለም በብዙ መልኩ ተለዋውጦ ነው ያገኙት።

በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ቃል የገቧቸውን አንኳር ጉዳዮች ለማሳካት ምን ሊሰሩ እንዳሰቡ የሚያሳውቁት አሁን ነው። የኑሮ ውድነት፣ የስደተኞች ጉዳይ፣ ግብር፣ የተሻለ የህዝብ አገልግሎት ወዘተ ቅድሚያ ሰጥተው የሚሰሩባቸው ጉዳዮች እንደሆኑ ተደጋግሞ ተነግሯል።

ምንም እንኳን የአገር ውስጥ ጉዳዮች ቅድሚያ ቢሰጡም የውጭ ግንኙነታቸውን ማሻሻልም ቀዳሚ ከሆኑት አጀንዳዎቻቸው ውስጥ አንዱ ነው። እንግሊዝ ከበርካታዎቹ የአፍሪካ አገራት ጋር ካላት ታሪካዊና የባህል ግንኙነት አንጻር በውጭ ግንኙነቷ ትኩረት ከምትሰጣቸው አህጉራት ቀዳሚው አፍሪካ ነው።

በአዲሱ የሌበር መንግስት እንግሊዝ በአፍሪካ ልታካሂደው ያቀደችው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከኮንሰርቫቲቮቹ የተለዬ እንደሚሆን መረጃዎች እያመላከቱ ነው።

አዲሱ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪዬር ስታርመር ተራማጅ ሪያሊዝም (progressive realism) የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንደሚከተል የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቅሳሉ። ውስብስቡንና አስቸጋሪውን የዓለም ግኦፖለቲካዊ መልከ ዓምድር እንደ ሁኔታዎች የሚለዋወጥ (ፕራግማቲክ) ግበረገባዊ አካሄድን የሚከተል ነው።

በዚህ ረገድ በዓለም መድረክ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሚናዋ እያደገ የመጣችው አፍሪካን የሚመጥንና የሚስማማ ፖሊሲ መቅረፅ የሌበር መንግት ዋነኛ ትኩረት እንደሚሆን እየተገለጸ ነው። ሌበሮች አፍሪካን ከዚህ በፊት በሚያዩበት መነፅርና የግንኙነት ዓይነት ሊቀጥሉ እንደማይችሉ የተገነዘቡ ይመስላሉ።

የስታርመር መንግስት ከአፍሪካ ጋር ለሚኖረው ግንኙነት ጸጥታ፣ ፍልሰት፣ ንግድና ኢኮኖሚ፣ ሰብዓዊ መብቶችና ዲሞክራሲ እንዲሁም የባለ ብዙ ወገን የፋይናንስ ተቋማት ትኩረት የሚያደርግባቸው ዘርፎች ስለመሆናቸው ተጠቅሷል። እንግሊዝ በአፍሪካ የምትከተለው ፖሊሲ ሁለቱን አካላት የተሻለና በእኩል መርህ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ተብሏል።

ዘሳውዝ አፍሪካን ታይምስ እንደዘገበው ሌበር በማኒፌስቶው የአፍሪካን እያደገ የመጣ ተፅእኖ መገንዘቡንና ለዚህ የሚጣጣም ወቅቱን የዋጀ አዲስ አቅጣጫ ለመከተል ማቀዱን አስፍሯል።

በአህጉሪቱ የሕግ የበላይነት፣ ዲሞክራሲና ዘላቂ ልማት የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የትኩረት ነጥቦች መሆናቸው ነው የተጠቀሰው። በአጠቃላይ በፀጥታ፣ ንግድ፣ ዓለም አቀፍ ሕግ የአዲሱ መንግስት ጥቅል ስትራቴጂያዊ የትኩረት ዘርፎች ይሆናሉ ተብሏል።

በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት አካባቢ በማደግ ላይ ያሉ አገራትን ግምት ውስጥ ያስገባ እና የተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራርና ማሻሻያ እንዲኖር እንግሊዝ ባላት ተፅእኖ ድጋፍ ማድረግም ሌላ የትኩረት አቅጣጫ ነው።

የስደተኞች ፖሊሲ በቅድመ ምርጫ የእንግሊዝ ፖሊቲካ ሰፊ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል። በዚህ ረገድ የሩዋንዳ ዕቅድ በመባል የታወቀውና በህገ ወጥ መንገድ እንግሊዝ የገቡ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመመለስ የወጣው ህግ የአገሪቱን ፖለቲከኞችና ህዝብ ሲያከራክር ቆይቷል። የስታርመር መንግስት ስልጣን በያዘ ማግስት ህጉ እንደማይሰራ አስታውቆ የተሻለ ፖሊሲ ይዞ እንደሚመጣ ቃል ገብቷል።

ስደተኞች ለእንግሊዝ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉና ሰፊ የሰለጠነና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎት ስላለ የፋይናንስና ቢሮክራሲ አሰራሮችን በማሻሻል የአጭር ጊዜ ቪዛ ጭምር በመስጠት የጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል።