አዲስ ተመራጮች ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ሀብት ስለማስመዝገብ

መስከረም 5/2014 (ዋልታ) በ2014 ዓ.ም ሁሉም ተመራጭ የህግ አስፈፃሚ፣ አስተርጓሚና የህዝብ ተወካዮች አባላት ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ሀብት እንደሚያስመዘግቡ በፌደራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሃብት ማሳወቅና ምዝገባ ዳይሬክተር መስፍን በላይነህ ገለጹ።

ኮሚሽኑ የ2013 ዓ.ም አፈፃፀምን በመገምገም የ2014 ዓ.ም ተግባራትን ይፋ አድርጓል።

በዋናነትም የሃብት ማሳወቅና ማስመዝገብ ሥራ በበጀት ዓመቱ ውጤት የተገኘበት መሆኑ ተመላክቷል።

በግምገማው 31 ሺሕ 13 ተቋማት መረጃ መሰብሰቡ፣ 2 ሚሊየን 46 ሺሕ 283 ሰራተኞችና አመራሮች መኖራቸው መረጋገጡ እንዲሁም በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ሃብት የማሳወቅ አዋጅ መውጣቱ ተገልጿል።

ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ከነበሩት በተጨማሪ ከ115 በላይ ህዝባዊ ድርጅቶች ማለትም የፋይናንስ ተቋማት፣ አክሲዮኖችና ኢንዶውመንቶች የሃብት ማሳወቅ ምዝገባ ተከናውኗል ነው የተባለው።

ሀብት ካስመዘገቡት 705 ሃብት አስመዝጋቢ መካከል በተደረገ የትክክለኛነት ማረጋገጥ ሂደት 47 በመቶ የሚሆኑት የተሳሳተ መረጃ መስጠታቸውም ተጠቁሟል።

13 ግለሰቦች ሀብት የሸሸጉ ሲሆን፣ ከ390 በላይ መረጃዎች ለፖሊስና ዓቃቤ ህግ ተላልፏልም ተብሏል።

በተስፋየ አባተ