አዲስ አበባ እንደ አውሮጳዊያኑ አቆጣጠር 2021 በዓለም ላይ መጎብኘት ካለባቸው ምርጥ ቦታዎች አንዷ መሆኗን ታዋቂው የአሜሪካ የጉዞ መጽሔት “ኮንዴ ናስት ትራቭለር” ገለፀ።
መፅሄቱ “ከተማዋ እንደ ስሟ እየሆነች መጥታለች” ብሏል።
መቀመጫውን ኒውዮርክ ያደረገው ታዋቂው የጉዞ መጽሔት እንደዘገበው በቀጣዩ የአውሮጳዊያን ዓመት በዓለማችን መጎብኘት አለባቸው ያላቸውን 21 ምርጥ ቦታዎች ይፋማደረጉን ኢዜአ ዘግቧል።
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተጣሉ ገደቦች ምክንያት እየተጠናቀቀ ባለው የአውሮጳዊያኑ ዓመት ሰዎች እንደልባቸው መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ መጽሔቱ አስታውሷል።
በዓመቱ ውስጥ ሰዎች ጉዞ ባያደርጉም ለጉዞ ያላቸው ፍላጎትና ጉጉት አሁንም እንዳልተገታና ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ የሚገባው አዲሱ ዓመት ዳግም ወደ ጉዞ የሚገቡበት ይሆናል ብሏል።
“ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ስምና ዝና እየጨመረ መጥቷል” ያለው መጽሔቱ፤ እንደ አውሮጳዊያን አቆጣጠር በ2017 መጨረሻ የተጀመረው የኤሌክትሮኒክስ ቪዛ አገልግሎት አገሪቷን ለመጎብኘት ያለውን ሂደት እንዳቀለለውና የቱሪዝም ዘርፍ 48 ነጥብ 6 በመቶ ዕድገት እንዲመዘግበት ማድረጉን ገልጿል።
መፅሄቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኖቤል የሠላም ሽልማት ማግኘታቸው የዓለምን ትኩረት መሳቡን አንስቷል።
ጎብኚዎች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም /ዩኔስኮ/ ዘጠኝ የሚዳሰሱ ቅርሶች የተመዘገበላትን ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ሲመጡም አዲስ አበባን መዳረሻቸው እንዲያደርጉም ጠቁሟል።
ባለፈው ዓመት የተከፈተው ባለ ብዙ ገጽታው የአንድነት ፓርክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በተሰራው ቤተ መንግስት ቅጥር ግቢ 16 ነጥብ 2 ሄክታር ቦታ መያዙን ገልጿል።
ጎብኚዎች በፓርኩ በሚገኙ በግድግዳ የስነ-ጥበብ ስራዎች፣ አገር በቀል እፅዋትና የተቀረጹ ምስሎች በያዙ የአትክልት ስፍራዎች መጓዝ ይችላሉ፤ የዘጠኙን ክልሎች ባህል የሚያሳዩ ድንኳኖችንም ይመለከታሉ ብሏል።
“በጥላ ውስጥ ያሉ ፊቶች” የኢትዮጵያን ታሪክ በጥልቅ የሚዳስስና የንጉሳዊውን ስርዓት የገለበጠው የደርግ መንግስት፣ የቀይ ሽብር ጊዜና የደርግ የፖለቲካ እስረኞች የደረሰባቸውን ስቃይ እንደሚያሳይ ያትታል።
መፅሄቱ በአዲስ አበባ በስተሰሜን በኩል 20 ደቂቃ ከተጓዙ በኋላ ለአየር ንብረት ተስማሚ፣ አዲስ ፈጠራ የታከለበት የመዝናኛና የማረፊያ ቦታ የእንጦጦ ፓርክ እንደሚገኝም ይገልጻል።
በባህር ዘፎች በተከበበውና በ1 ሺህ 295 ሄክታር መሬት ላይ የተንጣለለው የእንጠጦ ፓርክ በውስጡ ረጅም ርቀት ጉዞ የሚደረግባቸው ቦታዎች፣ የብስክሌትና የፈረስ መጋለቢያ ስፍራዎች፣ ዒላማ መተኮሻ፣ የቡድን ተኩስ ስፖርት መጫወቻ /ፔይንትቦል/፣ የመወዳደሪያ መኪኖችና በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የገመድ ወይም ኬብል ላይ መጓጓዣ ስለመኖሩም ጠቅሷል።
ጎብኚዎች በእንጦጦ ፓርክ ምሽቱን በኩሪፍቱ ሪዞርት በማሳለፍ በኮከብ ከደመቀችው ሰማይ ስር ሆኖ በፓርኩ በተዘጋጁት አነስተኛ የድንኳን ማደሪያዎች ጊዜ ማሳለፍ እንደሚችሉ መጽሔቱ አመልክቷል።
በተጨማሪም አዲስ አበባን መጎብኘት ማለት ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በሚገኘው “የዓለማችን የመጀመሪያው ከንኪኪ ነጻ የተጓዦች ተርሚናል” ማለፍ እንደሆነና የተርሚናሉ ግንባታ ለብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ትኩረት መስጠቱን ይገልጻል።
ባለፈው ዓመት የተከፈተው የኢትዮጵያን እምቅ የእስልምና ሃይማኖት ቅርሶችን የያዘው ቢላሉል ሐበሺ ሙዚየምም በመዲናዋ ይገኛል ብሏል።
የፓርኮች ግንቦታ መጀመሩ ከተማዋ በያዘችው ፍጥነት መጓዟን እንደምትቀጥል እንደሚያሳይ ጠቅሶ አዲስ አበባ ‘ከአስርት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ስሟ እየኖረች ነው ይላል መጽሔቱ በዳሰሳው።
የአሜሪካው ታዋቂ የጉዞ መጽሔት ኮንዴ ናስት ትራቭለር አንጎላና ጋናን ከአፍሪካ መጎብኘት ያለባቸው በማለት የምርጥ ቦታዎች ዝርዝር ውስጥ አካቷቸዋል።
ኒው ዮርክ ከተማ፣ ሂልድስበርግ,ካሊፎርኒያ፣ ቤርሙዳ፣ ቺያፓስ /ሜክሲኮ/፣ ኪዮቶ /ጃፓን/፣ ኖቫ ስኮቲያ /ካናዳ/፣ ኢጣሊያ፣ ኦስሎ /ኖርዌይ/፣ ጠረፋማ የእንግሊዝ አካባቢዎችና ሆኪያንጋ /ኒውዚላንድ/ መጎብኘት አለባቸው ከተባሉት 21 ምርጥ ቦታዎች ውስጥ ይገኙበታል።
በኮንዴ ናስት ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ኩባንያ የሚተዳደረው የአሜሪካ ታዋቂ የጉዞ መጽሔት ከ33 ዓመታት በፊት መቋቋሙን መረጃዎች ያመላክታሉ።