አዲስ አበባ ተወዳዳሪ በሚያደርጋት ሁኔታ እያደገች ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ነሐሴ 29/2016 (አዲስ ዋልታ) አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በሚያደርጋት ሁኔታ በፍጥነት እያደገች መሆኗን የከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ፎረሙ “ዘላቂ የከተሞች ልማት ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ 2063” በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል ፓን-አፍሪካን አዳራሽ እየተካሄደ ነው፡፡

በመጀመሪያ የአፍሪካ ከተሞች ፎረም ማስጀመሪያ ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከመላው አፍሪካና ሌሎች ሀገራት ለተውጣጡ እንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ብቻ ሳትሆን የፓን አፍሪካን ንቅናቄ የተወለደባት የአፍሪካ ነፃነት ቀንዲል መሆኗን ገልጸዋል።

“ከንቲባነት የከተማ መሪነት አስኳል ነው” ያሉት ከንቲባዋ ከሁሉም በላይ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ አበባ ለማድረግ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቅርብ መሪነትና መላው የከተማችን አመራር የተቀናጀ ርብርብ ውጤታማ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

በአመራር ዘመናችን የመንግሥት እና የህዝብ አቅሞችን በማስተባበር ከተማን መለወጥና አቅሞችን አስተባብሮ ማልማት እንደሚቻል አረጋግጠናል ያሉት ከንቲባ አዳነች በተለይም ባለፉት ዓመታት ሰው ተኮር አቅጣጫን ተከትለን ስለሰራን የዜጎችን ህይወት በተጨባጭ የሚለውጡ ስራዎች ማከናወን ችለናል ሲሉም ተናግረዋል።

ለአብነት የተማሪዎች እና ማህበረሰብ ምገባዎች መመስረት፣ የቅድመ-ልጅነት እድገት ማዕከላት መስፋፋት፣ የሴቶች የተሃድሶና የክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከላት መገንባትና ለወጣቶች ሰፋፊ የስራ ዕድሎችን መፍጠር እንዲሁም በዋናነት በስራዎቻችን ሁሉ ህዝቡን ለማገልገል ቅድሚያ መስጠታችን ማሳያዎች ናቸው ማለታቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

ታዳሚዎቹ ከፎረሙ ጎን ለጎን በአዲስ አበባ የተገነቡ ሜጋ ፕሮጀክቶችንና የቱሪዝም መዳረሻዎችን እንደሚጎበኙና የተለያዩ በከተማ ልማት ላይ የካበተ ልምድ ያላቸውና በምርምር ዘርፉ የላቀ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ምሁራን ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀርባሉ ተብሎም ይጠበቃል።

በፎረሙ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ 49 የሚደርሱ የአፍሪካ አገራት ተወካዮች እንዲሁም ከ30 በላይ የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች፣ ሚኒስትሮችና አምባሳደሮች እየተሳተፉ ይገኛል።