ሐምሌ26/2016(አዲስ ዋልታ) አዲስ አበባ እና የቻይናዋ ር ጃው ከተማ የእህትማማችነት ግንኙነት ለመመስረት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመዋል፡፡
ስምምነቱን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ እና የር ጃው ከተማ ምክትል ከንቲባ ዣንግ ዲአንሁ ናቸው የፈረሙት።
የር ጃው ከተማ ልዑካን ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ባካሄዱት ውይይት ር ጃው ያላት ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ፣ የከተማ ፕላን እና የኢኮኖሚ እድገት ስኬት ተነሳሽነትን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከተማዋ ለአረንጓዴ ልማትና ኢኖቬሽን ያላት ቁርጠኝነት አዲስ አበባ ካላት ራዕይ ጋር ትስስር አለው ያሉት ምክትል ከንቲባው ካላችሁ ምርጥ ተሞክሮ ለመማር እና ለሁለቱም ከተሞች በሚጠቅሙ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት ፍላጎት አለን ብለዋል።
በሁለቱ ከተሞች መካከል የእህትማማችነት ግንኙነት ለመፍጠር የተደረሰው የመግባቢያ ስምምነት በዘላቂ ልማት፣ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ፣ በባህል፣ በንግድ፣ በትምህርት እና ጤና መስኮች በትብብር ለመስራት እና የጋራ ብልጽግና እና ልማትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ እምነት እንዳላቸው ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ ገልጸዋል።
ከከንቲባ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ እነደሚያመለክተው የር ጃው ከተማ ምክትል ከንቲባ ዣንግ ኢትዮጵያ እና ቻይና ካላቸው የረጅም ጊዜ ጠንካራ ግንኙነት ባሻገር በ ር ጃው ከተማ የሚገኙ አምራች ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ የንግድ አጋሮቻቸው ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡
አክለውም የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ሁለቱ ከተሞች በተለያዩ መስኮች የሚኖራቸውን ትብብር ያጠናክራል ብለዋል።