መጋቢት 23/2013 (ዋልታ) – አዲስ የተሾሙ የካናዳ፣ የእስራኤል እና የባንግላድሽ አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤያቸውን ቅጂ ያቀረቡትን አቶ ፌይሰል አሊይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል በቢሮያቸው ተቀብለዋል።
አዲሱ የካናዳ አምባሳደር ስቴፋን ጆቢን በስነ-ስራዓቱ ላይ ሁለቱ ሀገራት በጣም ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው አውስተው፤ ይህንንም በንግድ፣ በፖለቲካ እና በሌሎች ዘርፎች ለማሳደግ ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ ክልል ስላለው የሰብዓዊ ድጋፍ፣ የኮቪድ ክትባት እና የኦኮኖሚ ጉዳዮች ዙሪያ ተነጋግረዋል።
በሌላ በኩል አዲሱ የእስራኤል አምባሳደር አለሊ አድማሱ ሁለቱ ሀገራት የረጅም ጊዜ ታሪካዊና ሀይማኖታዊ ዳራ ያለው ግንኘነት እንዳላቸው አውስተው፣ የሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች ግንኙነት የላቀ ለማድረግ ተግተው እንደሚሰሩ ገልፀዋል።
ዳይሬክተር ጄነራሉ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከእስራኤል በመስኖ እርሻ፣ በኢንቨስትመንት፣ በንግድ እንዲሁም በቱሪዝም ዙሪያ ብዙ የምትቀስማቸው ልምዶች እንዳሉ ገልፀው ፤በእነዚህ ዘርፎች ላይ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ከአምባሳደሩ ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ገልፀዋል።
እንደዚሁም አዲሱ የባንግላዴሽ አምባሳደር ክቡር ናዝሩል ኢስላም፣ በበኩላቸው አትዮጵያ የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ በሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ፣ ኢንቨስትመንት እና ንግድ ላይ አብሮ ለመስራት የሚያስችል አቅም እንዳለ ገልጸው ይህንን ለማሳካት ጠንክረው እንደሚሰሩ መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡