አገልግሎቱ ከወንጀል ተግባር ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎ የጠረጠራቸውን 665 የባንክ ሂሳቦችን አገደ

መስከረም 30/2015 (ዋልታ) የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ከወንጀል ተግባር ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎ የጠረጠራቸውን 665 የባንክ ሂሳቦችን አገደ።

አገልግሎቱ ለዋልታ በላከው መግለጫ ከህገ-ወጥ የውጭ አገራት ገንዘብ ማስተላለፍ ወንጀሎች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ 665 የባንክ ሂሳቦች እንዳይንቀሳቀሱ ማገዱን ነው ያስታወቀው።

በአገልግሎቱ የታገዱት የባንክ ሂሳቦቹ ህጋዊ የውጭ አገራት ገንዘብ ማስተላለፍ ፈቃድ ሳይኖራቸው በህገ-ወጥ መንገድ በሀገር ውስጥ እና በውጭ አገራት ካሉ አካላት ጋር ትስስር በመፍጠር በህገ-ወጥ መንገድ የገንዘብ ማስተላለፍ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ ሲሆኑ በወንጀል ድርጊቶቹ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተሳትፎ የነበራቸውን አካላት በህግ ተጠያቂ ለማድረግ የተጠናከረ ሥራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝም ጨምሮ ገልጿል።

የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን በመፈፀም የተገኘን ሃብት ከህጋዊ ምንጭና በህጋዊ መንገድ የተገኘ በማስመሰል የመጠቀም ወንጀሎች አፈፃፀም በየጊዜው እየተቀያየረ ያለ ወንጀል ከመሆኑም ባሻገር ከወንጀል ድርጊቶቹ የተገኘው ሃብት ሽብርተኝነትን በገንዘብ ለመርዳት ወንጀል መፈፀሚያ ጭምር የሚውል በመሆኑ የመከላከልና መቆጣጠር ስራው በተጠናከረ አግባብ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እነዚህን ወንጀሎች ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚያደርገው ሂደት ህብረተሰቡ መረጃና ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርቧል።