ጥቅምት 4/2015 (ዋልታ) በኢትዮጵያ የሚገኙ አገልግሎት የማይሰጡ ቁርጥራጭ ብረቶች በቀጥታ ግዥ ለብረት ኢንዱስትሪዎች ብቻ እንዲሸጥ ተወሰነ።
የማዕድን ሚኒስቴር እና የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን በመንግሥት ተቋማትና በግለሰቦች ደረጃ የተከማቹ አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶች አወጋገድ በተመለከተ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ያለአገልግሎት የተከማቹ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች፣ የማያገለግሉ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች ለብረታ ብረት አቅላጭ ኢንዱስትሪዎች ብቻ በሽያጭ እንዲቀርቡ መወሰኑ በመግለጫው ተመላክቷል።
ያገለገሉ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች በኪሎ 21.15 ብር የሚቀርቡበት ዋጋ በ51.25 ብር የተተካ ሲሆን በውዳቂ ብረታ ብረትነት የሚወገዱ ተሽከርካሪዎችንና ማሽነሪዎች ደግሞ ይሸጡበት ከነበረው 31.18 ብር የ39.1 በመቶ የዋጋ ማስተካከያ ተደርጎባቸው በ51.25 ብር በኪሎ ይሸጣሉ ተብሏል፡፡
ከዚህ ቀደም ቁርጥራጭ የሆኑ ስቲል ብረታ ብረቶችን በኪሎ 29.30 ብር እንዲያስረክቡ የተገለጸላቸው መሥሪያ ቤቶች በአዲሱ ማስተካከያ በ64 ብር ሲያስረክቡ፣ በኪሎ 21.25 ብር ሲሸጡ የቆዩትን የካስት አይረን ብረቶች ደግሞ በ51.75 እንዲሸጡ መወሰናቸው ተመልክቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በኪሎ 108.65 ብር ይሸጡ ተብሎ ዋጋ የወጣላቸው ቁርጥራጭ አልሙኒየሞች፣ ከመስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በ120 ብር እንዲሸጡ ተወስኗል፡፡
ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ተሽከርካሪዎች ለብረት አምራች ኢንዱስትሪዎች በሽያጭ እንዲተላለፉ መንግሥት መወሰኑ የብረት አምራች ፋብሪካዎችን የግብዓት እጥረት በከፍተኛ መጠን የሚያቃልል መሆኑን ለፋብሪካዎቹ ትግበራውን የሚያስፈፅሙት ተቋማት የማዕድን ሚኒስቴር እና የገንዘብ ሚኒስቴር መሆኑም ታውቋል።
የማዕድን ሚኒስቴር በመንግሥት ተቋማት የተከማቹና አገልግሎት የማይሰጡ ብረታ ብረቶች ለሁሉም የብረት አምራች ፋብሪካዎች ለብረት አምራች ኢንዱስትሪዎች በሽያጭ መተላለፉ ሀገሪቱ በየዓመቱ ለብረት ግዥ የምታወጣውን ወጪ ለመቀነስ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሏል።
በደረሰ አማረ