አገር በቀል የእርዳታ ድርጅቶች የድርቅ ምላሽን በማካተት እቅዳቸውን እንዲከልሱ ጥሪ ቀረበ

የካቲት 21/2014 (ዋልታ) ከድርቁ ስጋትና ስፋት አንፃር እንዲሁም ተጠባቂው ዝናብ በወቅቱ ካልዘነበ ሊያጋጥም የሚችለውን የበጀትና የዓይነት ክፍተት ለመሙላት አገር በቀል የእርዳታ ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት የድርቅ ምላሽን በማካተት እቅዳቸውን እንዲከልሱ የሶማሌ ክልል ጠይቋል።

የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን እና የፋይናንስ ቢሮዎች በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ አገር በቀል የእርዳታ ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በክልሉ የተከሰተውን ድርቅ አስመልክቶ በጅግጅጋ ከተማ ውይይት አድርገዋል።

በምክክሩ ተሳታፊ የሆኑ አገር በቀል የእርዳታ ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት አመራርና ተወካዮች የክልሉ መንግሥት ድርቁ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የሰራቸውን ሥራዎችን አድንቀው በቀጣይ የልማት ዕቅድና ፕሮግራማቸውን አስተካክለው ከመንግሥት ጋር በመናበብ በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

በድርቁ ምክንያት በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ የቤት እንስሳት መሞታቸው ተጠቅሷል።

በክልሉ 40 ሺሕ አባወራዎች ከነቤተሰባቸው መፈናቀላቸው የተጠቀሰ ሲሆን 196 ሺሕ 875 ተማሪዎች ትምህርት አቋርጠው ከቤተሰቦቻቸው ጋር መሰደዳቸውም ተገልጿል።

በዚህም 388 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው በጥናት መረጋገጡን የክልሉ የፋይናንስ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሙሁየዲን አብዲ አስታውቀዋል።

በቀጣይም በክልሉ ለ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች ከውሃና መድኃኒት በተጨማሪ ወደ 374 ሜትሪክ ቶን የዕለት ደራሽ ሬሽን እንደሚያስፈልግ እና ለእንስሳትም የመኖና የውሃ አቅርቦት ያስፈልጋል መባሉን ከክልሉ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።