አገር አቀፍ የትምህርት ዘርፍ አማካሪ ምክር ቤት ተቋቋመ

አገር አቀፍ የትምህርት ዘርፍ አማካሪ

ኅዳር 14/2014 (ዋልታ) አገር አቀፍ የትምህርት ዘርፍ አማካሪ ምክር ቤት መቋቋሙን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) የአማካሪ ምክር ቤቱ መቋቋም በመጪዎቹ አምስት ዓመታት እንደ አገር የትምህርት ጥራት ያሉበትን ችግሮች ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ለመፍታት ያስችላል ብለዋል፡፡

አማካሪ ምክር ቤቱ በትምህርት ጥራት ላይ የሚደረጉ ሀሳቦችን በሙያዊ ዓይን እየገመገመ እና በሴክተሩ የሚሰሩ ስራዎችን እየተከታተለ ከሙያ አንጻር ሚኒስቴሩን የማማከር እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የአማካሪ ምክር ቤቱ በንዑሳን ዘርፎች በውስጥ የሚደራጅ ሆኖ ለጊዜው 20 አባላት እንደሚኖሩና ሰፊ ልምድ ያካበቱ እንዲሁም በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ምሁራን የተካተቱበት እንደሆነ ተገልጿል።

የምክር ቤቱ አባላት ቀጣይ በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍና  ከፍተኛ ትምህርት በንኡሳን የለውጥ ጉዳዮች ሚኒስቴሩን በማማከር ለሀገሪቱ የትምህርት ጥራት መጠበቅ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡