አፈ ጉባኤው በፓርላማው ተልዕኮ ዙሪያ ምርምር በማካሄድ ሥራዎችን እናዘምናለን አሉ

ሰኔ 17/2014 (ዋልታ) በፓርላማው ተልዕኮ ዙሪያ ምርምር በማካሄድ ሥራዎችን እናዘምናለን ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

ሁለተኛው ዓመታዊ የፓርላማ የምርምር ኮንፍረንስ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተካሂዷል።

የምክር ቤቱን አሰራር በምርምር ላይ በማስደገፍ የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖር የሚቆጣጠራቸው ተቋማትም በዚሁ አግባብ ታግዘው እንዲሰሩ የሚያስችሉ ጥናታዊ  ጽሑፎች ቀርበዋል።

አፈ ጉባኤው በተለይም ሕግ አውጪው በሥራው ሂደት እስካሁን የመጣበት መንገድና አሁን ሀገሪቷ በደረሰችበት ደረጃ የአሰራር ለውጦች የሚያስፈልጉት ስለመሆኑም አንስተዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው የሀገረ መንግሥት ግንባታው የተሳካ እንዲሆን በምርምር የተደገፉ ሥራዎች ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የተሻሉ ተቋማት እንዲፈጠሩ፣ የዜጎች ዋስትና እንዲረጋገጥ፣ የሕዝቡ አኗኗር እንዲቀየር ተቋማት ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ምክር ቤቱ በአሰራር፣ በሕግ አወጣጡና በአፈጻጸሙ እንዲጠናከር ምርምሩ የጎላ ትርጉም አለው ሲሉም ተናግረዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር ሥራውን በማገዝ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።