አፍሪካዊያን ያላቸው የባህል፣ እምነት እና ሥነ ጥበብ ልዩነት የጥንካሬ ምንጭ መሆኑ ተገለጸ

ጥቅምት 9/2015 (ዋልታ) አፍሪካዊያን ያላቸው የባህል፣ እምነት እና ሥነ ጥበብ ልዩነት የጥንካሬ ምንጭ መሆኑን የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

አፍሪካዊያንን በተለያዩ ዘርፎች የማቀራረብ ዓላማ ያለው “አፍሪካ ሰለብሬትስ” መርኃ ግብር ዛሬ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ መካሄድ ጀምሯል።

በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስትር ናሲሴ ጫሊ አፍሪካዊያን ያላቸው የባህል፣ እምነት እና ሥነ ጥበብ ልዩነት የጥንካሬ ምንጭ መሆኑን ተናግረዋል።

አፍሪካ በቱሪዝም ዘርፍ በርካታ ስጦታዎች ያሏት ቢሆንም እምብዛም አልተጠቀመችበትም ያሉት ሚኒስትሯ በተለይም አፍሪካዊያን እርስ በእርስ በመደጋገፍ የቱሪዝም ዝርፉን ሊያሳድጉት ይገባል ብለዋል።

አፍሪካዊያን ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን በመጎብኘት አኅጉሪቱን ማወቅ እንደሚገባቸውና የአፍሪካ ሰለብሬት መርኃ ግብርም እርስ በእርስ ለመተዋወቅ እድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የናይጄርያ አምባሳደር ቪክቶር አዴኩንሌ አዴሌኬ በበኩላቸው መርኃ ግብሩ የአፍሪካን የልዩነት ውበት በአንድነት የምናከብርበት መሆኑን ገልጸው በአፍሪካዊያን መካከል የኢኮኖሚ፣ ባህል እና ቱሪዝም ትስስርን ለማጠናከር ሰፊ ሚና እንደሚጫወት አመላክተዋል።

መርኃ ግብሩ በዛሬው እለት የኢትዮጵያ እና የተለያዩ አፍሪካ አገራት ባለስልጣናትና ተወካዮች በተገኙበት የአፍሪካዊያንን ቀጣናዊ የንግድ ትስስርን በተመለከተ የፓናል ውይይት በማድረግ ተጀምሯል።

የአፍሪካ ሰለብሬትስ መርኃ ግብር የተለያዩ አፍሪካዊ ቀለም ያላቸው ዝግጅቶችን አካቶ በአፍሪካ ህብረት ግቢ ውስጥ ለሦስት ቀናት እንደሚካሄድም ተገልጿል።

በሄለን ታደሰ