መስከረም 27/2014 (ዋልታ) ታንዛኒያዊ የሥነ-ጽሑፍ ባለሙያና ደራሲ አብዱልራዛቅ ጉርናህ (ፕሮፌሰር) የ2021 በሥነጽሑፍ ዘርፍ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ሆኑ።የሽልማት አካዳሚው ጉርናህን የቅኝ ገዢዎች ተፅእኖ እና በስደተኞች ዕጣ ፈንታ እንዲሁም በአህጉራት መካከል ያለው የባህሎች ልዩነት ዘልቆ ገብቶ በመስራቱ የተበረከተለት መሆኑ ተገልጿል።
ሽልማቱ በስዊድን አካዳሚ የሚሰጥ ሲሆን፣ 1 ነጥብ 14 ሚሊየን ዶላር እንደሚበረከትላቸው ተገልጿል፡፡
በ1948 ዛንዚባር ውስጥ የተወለደው ጉራና በ1960ዎቹ መገባደጃ ላይ ስደተኛ ሆኖ እንግሊዝ የገባ ሲሆን፣ እስካሁንም የ10 ልብ ወለዶች እና በርካታ አጫጭር ታሪኮች ደራሲ መሆናቸው በመረጃው ተጠቅሷል።
በቅርቡ በጡረታ እስኪሰናበቱ ድረስ በኬንት ዩኒቨርሲቲ ካንተርበሪ የእንግሊዝኛ እና የድህረ -ዘመን ሥነ-ጽሑፍ ፕሮፌሰር እንደነበሩ አስታውሶ ኢዜአ ዘግቧል።