አፍሪካ የራሷን ሚዲያ ማቋቋም እንዳለባት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አሳሰቡ

ጥር 29/2014 (ዋልታ) ዛሬ በተጀመረው 35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አፍካዊ የሆነ የሚዲያ አካል በኅብረቱ አማካኝነት እንዲመሰረት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዓለም ዐቀፍ ሚዲዎች አፍሪካን በጎ ባልሆነ መልኩ የረሀብ፣ እርስ በእርስ ጦርነት፣ ሙስና፣ በሽታ እና ድኅነት መገለጫ አድርገው በዓለም ዐቀፉ መድረክ ላይ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ዓለም ዐቀፍ ሚዲያዎች አፍሪካዊያን ራሳችንን የምናይበትን መንገድ ጨምር እያነፁ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህን የሚቀለብስ የሚዲያ አማራጭ በኅብረቱ አማካኝነት እንዲመሰረት ለጉባኤው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዚህም አኅጉሪቱ ላይ የሚሰነዘሩ የተዛቡ መረጃዎችን መዋጋት፣ የራሳችን አጀንዳ ማቅረብ እና የፓን አፍሪካኒዝም ድምፅን ማሰማት እንደሚቻል ጠቅሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ውስጥ መቆየቷን ለጉባኤው የገለፁ ሲሆን ሀገሪቱ ስታከናውነው በነበረው ህግን የማስከበር እንቅስቃሴ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳትን ለመቀነስ የተቻላትን ሁሉ ማድረጓን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር መንግስት የሀገሪቱን ሰላም ለመመለስ ያስችል ዘንድ ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር ይገኙ የነበሩ ግለሰቦችን ክስ ማቋረጡን እና አካታች የሆነ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድም ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የመስኖ ልማት እንቅስቃሴዎችን በማከናወን ለአርሶ አደሮቿ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገኘቷን እና ለሀገሪቱ ቀዳሚ የምግብ ዋስትና ስጋት የሆነው የደን መመናመንን በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አማካኝነት ስትመክት መቆየቷን በጉባኤው አውስተዋል፡፡
በዚህም በመጪው ክረምት አራተኛ ዓመቱን በሚይዘው በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአጠቃላይ 25 ቢሊዮን ችግኞችን ተክላ እንደምታጠናቅቅ መግለፃቸውን አቢሲ ዘግቧል፡፡