“አፍሮ ኒውስ” የተሰኘ አዲስ የዋልታ የቴሌቪዥን ቻናል የሙከራ ስርጭቱን ጀመረ

ሰኔ 28/2014 (ዋልታ) የዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት “አፍሮ ኒውስ” የተሰኘ አዲስ የቴሌቪዥን ቻናል የሙከራ ስርጭቱን ጀመረ፡፡

አዲሱ የቴሌቪዥን ቻናል በዋነኛነት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ስርጭት የሚያደርግ ሲሆን በተጨማሪም ለውስን ሰዓታት በአረቢኛና በኪስዋሂሊ ቋንቋዎችም ለአድማጭ ተመልካቾች ተደራሽ ይሆናል።

የዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ንጉሴ መሸሻ (ፒኤችዲ) አፍሪካ ገፅታዋን ለዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ በትክክለኛው መነፅር የሚያሳይ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚተላለፍ የቴሌቪዥን ቻናል ያስፈልጋታል ብለዋል፡፡

አዲሱን ቻናል በNSS12 ሳተላይት በ11 ሺሕ 605 ፍሪኩዌንሲ፣ ሲምቦል ሬት 45 ሺሕ ፖለራይዜሽን ሆሪዞንታል ብለው ያገኙታል፡፡

ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት በቅርቡ በሐረሪ ክልል የመጀመሪያውን የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በመክፈት ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

በቀጣይም ሁለተኛና ሦስተኛ ቅርንጫፎቹን በአፋርና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሚከፍት ይሆናል፡፡

ከአንድ ዓመት ወዲህ ደግሞ ከቴሌቪዥን መስኮት በተጨማሪ “በዋልታ ኤፍ ኤም 105.3” ሬዲዮ ሞገድም ለአድማጮች መድረስ ጀምሯል፡፡

1986 ዓ.ም ላይ ምስረታውን ያደረገው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል መጋቢት 24/2009 ዓ.ም ላይ ወደ ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ራሱን በማሳደግና አድማሱን በማስፋት በራሱ የቴሌቪዥን ቻናል ወደ ተመልካቾች መድረስ መጀመሩ ይታወሳል፡፡

በሳሙኤል ሓጎስ