ጥቅምት 18/2017 (አዲስ ዋልታ) ኢራን እስራኤል ድርጊቷን ከቀጠለች ውጥረቱ እንደሚባባስ ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዜሽኪያን አስጠነቀቁ።
የኢራን ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዜሽኪያን ኢራን ወደ ጦርነት መግባት አትፈልግም፤ ነገር ግን የሕዝቦቿን መብት በመጠበቅ እስራኤል ለፈጸመችው ጥቃት ተመጣጣኝ ምላሽ ትሰጣለች ብለዋል።
እስራኤል በኢራን ወታደራዊ ሳይቶች ላይ ከሰነዘረችው ጥቃት በኋላ ፕሬዝዳንት መሱድ የካቢኔ ስብሰባ ላይ የኢራን ሕዝብ ላለፉት 45 ዓመታት ለየትኛውም ጥቃት እንደማይበገር አሳይቷል ነው ያሉት።
ጥቃቱን ለመመከት አራት የአየር ክልል ጠባቂዎች መሰዋታቸውን አንስተው ኢራን ለእስራኤል ጥቃት ምላሽ የመስጠት መብት እንዳላት በአጽንኦት ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ በጋዛ እና ሊባኖስ ሕዝቦች ላይ እየተፈጸመ ስላለው እልቂት ሲናገሩ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የነጻነት እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነን የሚሉ አካላት ዓይተው እንዳላዩ እየሆኑ ነው ሲሉም ወቅሰዋል።
የእስራኤል መንግስት ድርጊቱን ከቀጠለ ውጥረቱ እንደሚባባስ አስጠንቅቀው አሜሪካ ጦርነቱ ይበልጥ እንዲስፋፋ እየደገፈች ነው በሚል መውቀሳቸውን የኢራን የዜና አገልግሎት ዘግቧል።