ኢቲዮ ቴሌኮም በሐዋሳ ያስገነባው ዲጂታል መማሪያ ማዕከል ተመረቀ

ሐምሌ 25/2014 (ዋልታ) ኢተዮ ቴሌኮም ደቡብ ሪጅን በሐዋሳ ከተማ አዳሬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያስገነባው ዲጂታል መማሪያ ማእከል የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፀጋዬ ቱኬ በተገኙበት በዛሬው እለት ተመርቋል፡፡
ተማሪዎች ተወዳዳሪና በቁ ዜጋ እንዲሆኑ እና ዓለም የደረሰበት ደረጃ እንዲደርሱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ዲጂታል ላይብረሪ መገንባት ወሳኝነት እንዳለው ከንቲባው ገልፀዋል፡፡
በኢቲዮ ቴሌኮም አማካኝነት በአዳሬ ሚሊኒየም ትምህርት ቤት የተጀመረው የዲጂታል መማሪያ ማዕከላት ግንባታ በቀጣይ በሌሎች ትምህርት ቤቶች ለማስፋት በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡
የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችን እጅግ ዝቅተኛ የሚባል መሆኑን የገለፁት ደግሞ የሀዋሳ ከተማ ትምህርት መመሪያ ኃላፊ ደስታ ዳንኤል ሲሆኑ ከመደበኛ ላይብረሪዎች በተጨማሪ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፉ ዲጂታል መማሪያ ማዕከሎችን ማስፋት ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ዲጂታል መማሪያ ማዕከሉ በ21 ኮምፒውተር፣ 21 ጠረጴዛ እና 21 ወንበር ከ11 ሜጋ ባይት የኢንተርኔት አገልግሎት ጋር በ690 ሺሕ ብር ወጪ የተገነባ መሆኑን የኢትዮ ቴሌኮም ደቡብ ሪጅን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሙጀዲን አብዱልቃድር ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም ኢቲዮ ቴሌኮም 1 ሺሕ 600 የፍራፍሬ ችግኞችን በመትምህርት ቤቱ በራሱ ወጪ መትከሉን የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ደጀኔ ገ/ሚካኤል ገልፀዋል፡፡
በማስጀመሪያ መርኃ ግብሩ የተገኙ የትምህርት ቤቱ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የላይብረሪ አገልግሎት ማግኘት መቻላቸው የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደሚያግዛቸው መግለጻቸውን የከተማው ኮሙዩኒኬሽን መረጃ ያመለክታል፡፡