ኢትዮጵያና ጣሊያን የ1.5 ሚሊዮን ዩሮ የእርዳታ ስምምነት ተፈራረሙ

ሚያዝያ 20/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያና በጣሊያን መንግሥታት መካከል የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ (የ82 ነጥብ 53 ሚሊዮን ብር) የእርዳታ ስምምነት ተፈረመ።
አዲስ አበባ በሚገኘው የጣሊያን ኤምባሲ በተፈረመው የእርዳታ ስምምነት ለምግብ አምራች ኢንዱስትሪዎች እና የምግብ ደኅንነትን ለማረጋገጥ ለታቀደው ፕሮጀክት የሚውል መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ፕሮጀክቱ በዘርፉ የተሰማራውን የሰው ሀይልና ቤተ-ሙከራዎችን በማጠናከር የምግብ ጥራትና ንጽህና መጓደልን ለመከላከል የሚያስችል ብሔራዊ የቁጥጥር ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል ሲሆን አዲስ አበባን ጨምሮ በ25 ዋና ዋና የሀገሪቱ ከተሞች ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል ተብሏል።
የእርዳታ ስምምቱን የገንዘብ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ትብብር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው እና በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር አጎሲቲኖ ፓሌሴ ፈርመውታል።