ጥቅምት 30/2014 (ዋልታ) የአገር መከላከያ ሠራዊትን ለመደገፍና አሸባሪውን ሕወሓት በከፈተው ጦርነት የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም ትናንት ምሽት በአዲስ አበባ የገቢ ማሰባሰቢ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡
በዚህም በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ባለሀብቶች፣ የተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከ1 ቢሊየን 540 ሚሊየን 700 ሺህ ብር በላይ ማሰባሰብ መቻሉ ተገልጿል፡፡
በአንድ ጀምበር ከተሰበሰበው ብር መካከል የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር 1 ቢሊየን 23 ሚሊየን 581 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡
ቀሪውን በከተማዋ የሚገኙ ባለሀብቶች፣ የተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች ድጋፍ ማድረጋቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባዘጋጀውና በሸራተን አዲስ ሆቴል በተካሄደው የገቢ ማሰባሰብ መርሐግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰራዊት ግንባታ ስራዎች አስተባባሪ ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብረሃም በላይ፣ የሀይማኖት አባቶች እና ባለሃብቶች ተሳትፈዋል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ሁሉም ዜጋ ባለው አቅም አገሩን ደግፎና ጠብቆ የማሻገር ኃላፊነት አለበት ብለዋል።
ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ እውቀት ያለው በእውቀቱ፣ ጉልበት ያለው በጉልበቱ እያንዳንዱ ሰው ሰፈሩን፣ መንደሩን፣ ክልሉን፣ አገሩን ጠብቆ ኢትዮጵያን የማሻገር ሀላፊነት እንዳለበት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ በተባበረ ክንድ የተዘመተብንን ዘመቻ ለማሸነፍ በተባበረ ክንድ ሰላማችንን ለማረጋገጥ በጋራ መቆም ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
እያንዳንዱ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ አሁን ላለው አንገብጋቢ ጉዳይ እንደ ከዚህ ቀደሙ ጠያቂ ብቻ ሳይሆን ምላሽ ሰጪም እንዲሆን አደራ ልላችሁ እፈልጋለሁ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው አንዲት አገር ሉዓላዊ ሆና ልትቀጥል የምትችለው ባላት ጠንካራ መከላከያ መሆኑን ገልጸዋል።
“የተባበሩብን ላይ ካልተባበርን የተባበሩብንን ልንከላከል አንችልም” ያሉት ከንቲባዋ፥ የተቃጣብንን አገር የማፍረስ አደጋ በመተባበር እና በመተጋገዝ መቀልበስ ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል።
“የገጠመን ፈተና በተለያየ ጊዜ ገጥሞን ያውቃል፤ አሁንም ቢሆን እየፈተነን ያለው አሸባሪው ወያኔ ሳይሆን ጋላቢዎቻቸው ናቸው” ያሉት ደግሞ የመከላከያ ሠራዊት ግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ ናቸው።
ሌተናል ጄኔራል ባጫ ዛሬም ሽብርተኛውን ህወሓት በመጋለብ አገሪቷን ለመበተን የሚሰሩ አካላትን አሳፍረን ኢትዮጵያን እናስቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል።
“እንዲህ ያለ ፈተና በአገራችን በተለያየ ጊዜ ገጥሞን ያውቃል፤ አሁን እየፈተነን ያለው ሽብርተኛው ወያኔ አይደለም፤ እየፈተነን ያለው ጋላቢዎቻቸው ናቸው፤ እንደ ዓድዋው ድል ከአያት ቅድመ አያቶቻችን በወረስነው ወኔ ዛሬም ወያኔን ጋልበው ኢትዮጵያን ለመበተን የቋመጡትን ኃይሎች አሳፍረን ኢትዮጵያን እናስቀጥላለን ለዚህ እንዳትጠራጠሩ” ብለዋል።