ኢትዮጵያን ለማዳከም የተከፈተው ዘመቻ መልከ ብዙ ነው – ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ታኅሣሥ 16/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያን ለማዳከም የተከፈተው ዘመቻ መልከ ብዙ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኅልውና አደጋው በግልጽ ብቻ አይደለም በስውርም ይፈጸማል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ወታደራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የመረጃ ጦርነቶች የሚካሄዱብን በተቀናጀና በረቀቀ መልኩ ነው ብለዋል፡፡

እኛ እየመከትን ያለነው ውጊያውን ብቻ ሳይሆን ዘመቻውን ጭምር ነው፤ የዘመቻው ግንባሮችም ብዙዎች ናቸው፤ አንዳንዶቹ ፊት ለፊት የሚፈጸሙ ሲሆን፣ አንዳንዶቹም በወጥመድ መልክ የሚከወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

መንግሥት በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ኅልውና ላይ የተከፈተውን ግልጽና ረቂቅ ዘመቻ ለመመከትና ለመቀልበስ ብሎም በዘላቂነት የኢትዮጵያን አሸናፊነት ለማረጋገጥ የነደፈው ዕቅድ ሁለገብና ሁሉንም ግንባሮች ለመመከት የሚያስችል ስልት ነው ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ትላንት በመኅበራ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክ አመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያን ዘላቂነት ባለድል የማያደርግ አካሄድ ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለጠላቶቻችን ብርታትን የሚፈጥር፣ የሽብር ቡድኖች እድሜያቸውን የሚያረዝሙበትን ሰበብ እንዲያገኙ መፍቀድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አለፍ ሲልም በስሜት የሚወሰኑ ወታደራዊ ውሳኔዎች ሀገራችንን በተራዘመ ጦርነት አዙሪት ውስጥ እንድትዘፈቅ ያደርጋል ብለዋል፡፡