ኢትዮጵያን ለቅቄ የመውጣት ሃሳብ የለኝም – አሜሪካዊው የዎርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ብሔራዊ ዳይሬክተር

ታኅሣሥ 7/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያን ለቅቄ የመውጣት ሃሳብ የለኝም ሲል አሜሪካዊው የዎርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ብሔራዊ ዳይሬክተር ኤድዋርድ ብራውን ገለፁ፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫናን ለማሳደር እና ኢትዮጵያን በትርምስ ቀጣና ውስጥ የምትገኝ አስመስሎ ለማቅረብ ዜጎቹ በአስቸኳይ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ መስጠትን የሰርክ ተግባሩ አድርጎታል።
ነገር ግን የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ የተረዱ በርካታ አሜሪካዊያን ለጥሪው አዎንታዊ ምላሽን የሰጡ አይመስልም፡፡
የዎርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ብሔራዊ ዳይሬክተርም ከእነዚህ ውስጥ ሲሆን ባለፈው ሳምንት በአፋር ክልል፤ በዚህ ሳምንት ደግሞ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎችን ተዘዋውረው መመልከቱን ገልፀዋል።
በዛሬው ዕለት ደግሞ በአማሮ ፣ ገላና እና ሱሮበርጉዳ ወረዳ ዘለቄታዊ ሰላምን ለማምጣት በ500 ሺሕ ዶላር የሚተገበር ፕሮጀክት አስጀምረዋል።
ለዳይሬክተሩ የአሜሪካ መንግስት ዜጎቹ በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ እየወተወተ ይገኛል እርሶ እንዴት ጥሪውን ሳይቀበሉ ቀሩ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ያለሁት የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማገልገል ነው፤ ደግሞም በጣም በማስፈልግበት ሰዓት መሆን ያለብኝ እዚሁ ነው ብዬ አምናለሁ ሲሉ መልሰዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም በመላ አገሪቱ ከሕዝቡ እና ከመንግስት በኩል ከፍተኛ ድጋፍ ነው እየተደረገልን ያለው ስራዬን በአግባቡ እየሰራሁ ነው ስለዚህ ወዴትም አልሄድም ሲሉ ምላሽ መስጠቱን ከአሐዱ ቴሌቪዥን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።