ኢትዮጵያን ከምዕራባዊያን ተፅዕኖ ነፃ ማውጣት ላይ ያተኮረ ውይይት እየተካሄደ ነው

የካቲትት 24/2014 (ዋልታ) አፍሪካን እንዲሁም ኢትዮጵያን ከምዕራባዊያን ተፅዕኖ እንዴት ነፃ እናውጣ በሚል መሪ ቃል የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የውይይት እያካሄደ ነው።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ባለው ውይይት ኢትዮጵያ አሁን ላይ የተጋረጠባትን የውጭ ጫና እንዴት መቋቋም ይቻላል፣ በዲፕሎማሲው ዘርፍ አሸንፎ ለመውጣት ጠንካራ እና አሸናፊ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራትስ እንዴት ይቻላል? በሚል ጉዳይ ላይ ነው ውይይቱ ትኩረቱን ያደረገው።

ኢትዮጵያ እና የፀጥታው ምክር ቤት በሚል ኢትዮጵያ በፀጥታው ምክር ቤት ያላት ቦታ ምን ይመስላል የሚል ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

መድረኩን በይፋ የከፈቱት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዳምጠው ደርዛ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ለመቀራመት ያሰፈሰፉትን እንዳንድ ምዕራባዊያን አገራትን አሸንፋ ዛሬ ላይ በነፃነት የቆመች ሀገር ናት ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ ማሳያ የሚሆነው የመላው የጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነው የአድዋ ድል ምስክር መሆኑን ገልጸዋል።

ሜሮን መስፍን (ከአርባምንጭ)