ኢትዮጵያን ወደ አዲሰ ምዕራፍ ለማሻገር መንግስት፣ ፖለቲከኞችና ህዝቡ የጋራ ሃላፊነት እንዳለባቸው ተገለጸ

ኢትዮጵያውያን በችግር ውሰጥ ሆነው የአገራቸውን ሰላምና ሉአላዊነት በማስቀደም በድምጻቸው የመረጡት መንግስት በትላንትናው ዕለት ተመስርቷል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ፤ ኢትዮጵያ እንደፈረሰች አድርገው ሲያቀርቡ ለነበሩ የውሸት መረጃ አሰራጮች የመንግስት ምስረታው ትልቅ ትርጉም እንዳለው ለኢዜአ ተናግረዋል።

አዲስ ከተመሰረተው መንግስት ጋር በሰላም፣ በምጣኔ ሃብት፣ በህዝቦች አንድነት ላይ በማተኮር ከውስጥም ከውጭም የተደቀኑ ፈተናዎችን በድል ለመወጣት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የእናት ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ሰይፈስላሴ አያሌው (ዶ/ር) የመንግስት ምስረታው የፖለቲካ ልዩነትን ወደ ጎን በመተው ኢትዮጵያን በጋራ ለማሻገር የተዘጋጀ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

አዲስ የተመሰረተው መንግስት ከቀደሙት ስርአቶች መሰረታዊ ልዩነት ያለውና ሁሉንም አሳታፊ መሆኑን በተግባር ማሳየቱንም ተናግረዋል።

አገርን ማሻገር ለአንድ አካል የሚተው ባለመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተደራጀ መንገድ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ተስፋ አለኝ ብለዋል:ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ አስቸጋሪ ቢሆንም የብሩህ ተስፋ ምልክቶቹም የበዙ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የቀድሞው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ ናቸው።

በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል አስቸጋሪ ሁኔታ ቢኖርም ያለፉት ወራቶች ኢትዮጵያውያን በአንድነት ለሰላም የሰሩበት ወቅት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በልማት፣ በዴሞክራሲና ሌሎች ዘርፎች መንግስት የሚተገብራቸውን እቅዶች ውጤታማ ለማድረግ ዜጎች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

“ለአገራችን ወሳኞቹ እኛ እንጂ የውጭ ሃይሎች አይደሉም” የሚሉት አቶ አባዱላ ጫናዎችን በመቋቋም ለአገር እድገት መስራት ይኖርብናል ብለዋል።