ኢትዮጵያዊነት እጅግ የተጠናከረበት ወቅት ነው – አቶ ሺመልስ አብዲሳ

ነሃሴ 03/2013 (ዋልታ) – አሸባሪው የህወሃት ቡድን ኢትዮጵያዊነት የተዳከመ ቢመስለውም፤ ኢትዮጵያዊነት ግን እጅግ የተጠናከረበት ወቅት መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሺመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከፍተኛ ጥረት ያደረገ እና በማድረግ ላይ ቢሆንም በጀግኖቹ የኢትዮጵያ ልጆች ይህ ምኞቱ አይሳካም ብለዋል።

ይልቁንም ይህን አሸባሪ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ መቃብሩ ለመሸኘት መላው ኢትዮጵያዊያን በአንድነት መሰለፋቸውን አቶ ሽመልስ አስታውሰዋል።

ጀግናው የሃገር መከላከያ ሰራዊት እና መላው የፀጥታ ሃይል ኢትዮጵያን ለማዳን እየከፈሉ ላሉት መስዋዕትነት ላቅ ያለ ክብር አለን ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ለፀጥታ ሃይሉ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል።

ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ምድር ሃሰተኛ መንግስት እንደማይመሰረት አቶ ሽመልስ ገልፀው፤ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያጠናክርና በህዝብ የተመረጠ መንግስት በመጪው መስከረም ይመሰረታል ብለዋል።

አንዳንድ ጊዜ ያለፈባቸው አካላት ከተኙበት ሲነቁ የሽግግር መንግስት መመስረትን ቢመኙም በኢትዮጵያ ታሪክ ጠንካራው መንግስት ግን በመስከረም መባቻ ይፋ ይሆናል ሲሉ ገልፀዋል።

ክብር ሀገርን ከውጭ ወራሪና ከውስጥ ቦርቧሪ ለመከላከል መስዋዕትነትለሚከፍሉ የመከላከያ ሰራዊትና መላው የፀጥታ ሃይል ይሁን በማለት ንግግራቸውን ቋጭተዋል።

(በነስረዲን ኑሩ)