ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው ጥቅም መከበር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበ

ደመቀ መኮንን

መጋቢት 29/2014 (ዋልታ) በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከአሁን ቀደም ለሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅም መከበር ሲያደረጉት የነበረውን ሁሉን ዐቀፍ እንቅስቃሴ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአውሮፓ እና ካናዳ የኢትዮጵያ ሚሲዮን መሪዎች እና የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የበይነ መረብ ውይይት አካሂደዋል።

በውይይታቸው ወቅትም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ባለፈው አንድ ዓመት ያደረጉት ሁሉን ዐቀፍ እንቅስቃሴ ምስጋና የሚቸረው የዚህ ዘመን መልካም አብነት ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም ዳያስፖራው ለሀገሩ ብሔራዊ ጥቅም መከበር በርካታ ቁጥር ያለው ተሳታፊ በሁሉም አቅጣጫ እንዲንቀሳቀስ ያደረገበትን “የበቃ” እንቅስቃሴን በማሳያነት አቅርበዋል።

ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አሁንም በሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም ላይ ከባድ ስጋት የደቀኑ አጀንዳዎች እየተቀያያሩ የቀጠሉ በመሆናቸው ከአሁን በፊት ሲደረግ የነበረው የተቀናጀ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።

መንግሥት የሀገር ውስጥ ችግሮችን በመሠረታዊነት ለመፍታት የተለያዩ የተግባር እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋናነትም ሁሉን አካታቹ ብሔራዊ የምክክር መድረክ ኮሚሽን ተቋቁሞለት ኮሚሽነሮቹም ተሰይመውለት ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

መንግሥት በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የድጋፍ አቅርቦቱን ለማሳለጥና በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመታደግ ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ማቆሙን በሚመለከትም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

መንግሥት በማንኛውም አካባቢ ያሉ ዜጎች ችግር ውስጥ ሲወድቁ የመከላከል ኃላፊነት እንዳለበት ጠቅሰው ውሳኔውም የዚህ አንድ አካል ነው ብለዋል።

የሀገር ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና የሀገር ክብር መንግሥት የማይደራደርባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸው የሽብር ቡድኑ አሁንም ድረስ በወረራ ከያዛቸው የአፋር እና አማራ ክልሎች በአስቸኳይ ለቆ እንዲወጣ ግፊት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

መንግሥት በአጠቃላይ በሀገሪቱ ላይ የተደቀኑ ስጋቶችን ለመቀነስ የማስገንዘብ እና የማለዘብ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሆነና የኢትዮጵያን እውነታ በማሳወቁ እና በማስገንዘቡ በዚህ ወሳኝ ሂደት ላይ የዳያስፖራው ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ከአምባሳደሮች ጋር በቅርበት በመደማመጥ እና በመቀናጀት እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።

በዳያስፖራው እና በመንግሥት መካከል በመረጃ ክፍተት የተነሳ ልዩነት ሊፈጠር ይችላል ነገር ግን ቅድሚያ ትኩረት መደረግ ያለበት ቋሚ የሆነው የሀገር እና ሕዝብ ጥቅም ነው ብለዋል።

በየሀገራቱ ኢትዮጵያን የወከሉ አምባሳደሮችም ለዳያስፖራው ዋና የስበት ማዕከል በመሆን ከማዕከል በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት በዲፕሎማሲው መስክ በቀጣይ የተሻለ ሥራ መስራት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።

ያለፈውን ችግር እንዳለፍነው ሁሉ በእርግጠኝነት አሁንም እናልፈዋለን፤ ዋናው ጉዳይ በመደማመጥ እና በመናበብ ለሀገራችን እና ህዝባችን ብሔራዊ ጥቅም በጋራ ዘብ መቆም ነው ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡