ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በተለያዩ የማራቶን ውድድሮች ድል ተቀዳጁ

መጋቢት 25/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ዛሬ በተካሄዱ የተለያዩ የማራቶን ውድድሮች ድል ተቀዳጅተዋል።

በፈረንሳይ ፓሪስ ኢንተርናሽናል ማራቶን በወንዶቹ ዘርፍ አትሌት ጫሉ ዴሶ ገልሜሳ 2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ7 ሴኮንድ በሆነ ሰዓት በመግባት 1ኛ ወጥቶ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆኗል።

በዚህ ውድድር ተሳታፊ የነበረው ሌላኛው አትሌት ሰይፉ ቱራ 2ኛ ሆኖ በማጠናቀቅ የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል።

በሴቶች ዘርፍ አትሌት ፋንቱ ጂማ የቦታውን ሪከርድ ያሻሻለችውን ኬንያዊቷን አትሌት ጁዲት ጄፕቱምን ተከትላ በመግባት የብር ሜዳሊያ ስታሸንፍ አትሌት በሱ ሳዶ ደግሞ ውድድሩን በሦስተኝነት አጠናቅቃለች።

በባርሴሎና በተደረገ የወንዶች ግማሽ ማራቶን ውድድር አትሌት ሐፍቱ ተክሉ እና አትሌት ጫላ ረጋሳ በቅደም ተከተል 1ኛ እና 2ኛ በመውጣት የወርቅ እና የብር ሜዳሊያ አሸናፊ መሆኑን ኢብኮ ዘግቧል።

በባርሴሎናው የሴቶች ግማሽ ማራቶን ደግሞ አትሌት ጌጤ ዓለማየሁ 2ኛ አትሌት አስናቀች አወቀ 3ኛ እና አትሌት ረድኤት ዳንኤል 4ኛ ደረጃ በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቅቀዋል።

በሌላ በኩል በኮሪያ – ዴጉ ኢንተርናሽናል ማራቶን አትሌት ሽፈራው ታምሩ ውድድሩን በአንደኝነት በማጠናቀቅ የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፏል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW