ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር አካሄዱ

ጥር 23/2014 (ዋልታ) “ለወገን ደራሽ ወገን ነው” በሚል በእንግሊዝ ኖቲንግሀም ከተማ በሚኖሩ ኢትዮጵዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጅ ኤርትራዊያን ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር አካሄዱ።
ድጋፉ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት ያለመ እንደሆነና ወደፊትም በተመሳሳይ ፕሮግራሞች ድጋፍ የማሰባሰቡ ሥራ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡
የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለሰ የኮሙዩኒቲ አባላት በራሳቸው ፍላጎት ወገናቸውን ለመደገፍ ላሳዩት ከፍተኛ ተነሳሽነት አመስግነው ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አገር ናት፣ ሊበትኗትም ሆነ ሊያጠፏት ጥረት እያደረጉ ያሉ ኃይሎችን በጋራ መመከት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የማኅበራዊ ሚዲያ እየተራገቡ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት ከሚፈታተኑ አጀንዳዎች ራስን በመጠበቅ የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ እየተከናወኑ ለሚገኙ ተግባራት ድጋፍ መስጠት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
የመርሃ ግብሩ አስተባባሪዎች በበኩላቸው ኅብረታችንን በማጠናከር የተቸገሩ ወገኖቻችንን እናግዝ፣ ለአገራችን ሠላም በጋራ እንቀሳቀስ ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡