ሰመራ፣ ሰኔ 05/2013(ዋልታ) – ኢትዮጵያውያን በሁሉም በሚችሉት ቋንቋ ስለታላቁ ህዳሴ ግድብ ያለውን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያስረዱ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
“ዓባይ ወንዝን በፍትሃዊነትና በምክንያታዊነት ለመጠቀም የምሁራን ሚና” በሚል ሀሳብ በሰመራ ከተማ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩም የግብፅ እና የሱዳን ምሁራን እንዲሁም ዜጎች በሚችሉት ቋንቋ ሁሉ በግድቡ ዙሪያ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተሳሳተ መረጃን በመስጠት ላይ መሆናቸው በሃይማኖት አባቶች እና በሃገር ሽማግሌዎች ተገልጿል።
የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎችም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አንድ ልንሆን ይገባል፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሚችለው ቋንቋ ሁሉ ከህዳሴ ግድቡ ጋር ተያይዞ ያሉ እውነታዎችን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያስረዳ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አደም ቦሪ በአባይ ወንዝ ተጠቃሚነት ላይ እና በህዳሴ ግድብ አማካኝነት የሚደርሱብንን ጫናዎች በመመከት፤ ግድቡን በማጠናቀቅ ታሪክ ሰሪ ትውልድ ልንሆን ይገባል ብለዋል።
የግብፅ እና ሱዳን ምሁራን በግድቡ ዙሪያ ያገኙትን መገናኛ መንገድ ሁሉ በመጠቀም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተሳሰት መረጃን በመስጠት ኢትዮጵያ ላይ ጫና በማሳደር ላይ መሆናቸውንም አንስተዋል።
በግድቡ ዙሪያ ያለውን እውነታ ከማስረዳት አንፃር በተለይ በውጭ ሀገራት በሚገኙ ምሁራኖች የተሰሩ ስራዎች ዝቅተኛ መሆን ለግብፅ እና ሱዳን ምሁራን ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ነው ያነሱት።
በመሆኑም በዋነኛነ ግብፅ እና ሱዳን በተጨማሪ ደግሞ የውጭ ሀይላት ጫና በመበርታቱ ምሁራን ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
ምሁራን ሚናቸውን እንዲወጡ ለመቀስቀስ ባለመው በዚሁ መድረክም የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች የቀረቡ ሲሆን የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን እና የመንግስት ስራ ሀላፊዎችም ተሳትፈውበታል፡፡
(በትዕግስት ዘላለም)