“ኢትዮጵያ፤ ምድረ ቀደምት” የተሰኘ የትውውቅ መርኃ ግብር በዶሃ ተካሄደ

ሰኔ 16/2013(ዋልታ) – በዶሃ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኤምባሲ የኢትዮጵያን የባህል እሴቶች እና የቱሪዝም ሃብቶች የሚያስቃኝ “ኢትዮጵያ፤ ምድረ ቀደምት” የተሰኘ መርኃግብር አካሂዷል።
በኳታር ዶሃ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርስቲ ምሁራን እና ጋዜጠኞች በዝግጅቱ ተካፍለዋል፡፡
በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ በመርኃግብሩ ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ያላት እና ነጻነቷን አስከብራ የቆየች ሀገር ብቻም ሳትሆን፣ ለዓለም ያበረከተቻቸው የባህል፣ የታሪክ፣ የሥነ ጥበብ፣ የቋንቋ እና የሌሎች ሀብቶች ባለቤት መሆኗን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ 13 የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶችን እና ከ12 በላይ የታሪክ መዛግብትን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ ያስመዘገበች፤ መሆኗንም ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ሰፊ እና እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም ያላት በመሆኑ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሀገሪቱን እንዲጎበኝ ጥሪ ቀርቧል።
በመርኃ ግብሩ የኢትዮጵያን የባህል፣ የሃይማኖት፣ የታሪክ፣ የተፈጥሮ፣ የሥነ ጥበብ እና ሌሎች መስህቦችን የሚያስተዋውቅ ሰፊ ገለጻ ተሰጥቷል፡፡
የዝግጅቱ ታዳሚዎች ስለ ኢትዮጵያ ግንዛቤ እንደጨበጡ በመግለጽ ሀገሪቱን ለመጎብኘት ፍላጎት እንዳላቸው የተናገሩ ሲሆን በመርኃ ግብሩም ደስተኞች መሆናቸውን እንደገለጹ በዶሃ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኤምባሲ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡