ኢትዮጵያ ሀገሬ ናትና ከጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ጎን ነኝ – የሶሪያ ሬስቶራንት ስራ አስኪያጅ

ታኅሣሥ 11/2014 (ዋልታ) ሶሪያ ማንነቴና ትውልዴ ብትሆንም ኢትዮጵያ ሀገሬ ናትና ከጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ጎን ነኝ ሲሉ የሶሪያ ሬስቶራንት ስራ አስኪያጅ ረቢያ አላዲን ገለጹ፡፡
የሶሪያ ሬስቶራንት በመከላከያ ዋር ኮሌጅ ለሚገኙ የጦር ጉዳተኞች ሸዋርማ የተባለውን የሶሪያን ተወዳጅ ባህላዊ ምግብ በማዘጋጀት የምሳ ግብዣ አድርጓል።
ለኢትዮጵያ ያላቸው ፍቅር ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት አቶ ረቢያ አላዲን ይህንን ጀግና ሰራዊት ለማበረታታት በመቻሌ እድለኛ ነኝ ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ አመልክቷል።
ለሥራ ጉዳይ ኢትዮጵያ እመላለስ ነበር ያሉት ሶሪያዊው እዚህ ስመጣ ሀገሩንም ሕዝቡንም ወድጄው ኢትዮጵያዊት አግብቼ ኢትዮጵያዊ ሆኛለሁ፤ በዚህም ኩራት ይሰማኛል ብለዋል።
የሬስቶራንቱ ባለቤት ማህሌት አሰፋ ሶሪያዊው ባለቤታቸውና ሌሎቹም ሰራተኞች ህይወቱን ሳይሳሳ ሀገራችንን እያስቀጠለ ለሚገኘው ለአገር መከላከያ ሰራዊት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።