ሰኔ 24/2013(ዋልታ) – ኢትዮጵያ ለመንገድ ፕሮጀክቶች የሰጠችው ትኩረት ቀጣናውን ለማስተሳሰር ፋይዳው የጎላ መሆኑን የላፕሴት ኮሪደር ፕሮጀክት አባል አገራት ልዑካን ቡድኖች ገለጹ።
የላፕሴት (LAPSSET) ኮሪደር ፕሮጀክት ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ደቡብ ሱዳንን በትራንስፖርትና በሌሎች መሰረተ ልማቶች የሚያስተሳስር ፕሮጀክት ነው።
የፕሮጀክቱ አባል አገራት ልዑካን ቡድኑ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተመረቀውን የሞጆ – መቂ – ባቱ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክትን እና የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎብኝተዋል።
በዚህም አባል አገራቱ የኢትዮጵያ መንግስት ከጎረቤት አገራት ጋራ በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የልዕካን ቡድኑ አባላት አድንቀዋል።
በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አዲያኒካ አዲያሚ እንዳሉት፤ “ፕሮጀክቱ በአገራቱ መካከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ከማጠናከር ባሻገር የተቀላጠፈ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር ለማስቻል ትልቅ ጠቀሜታ አለው።”
የላፕሴት ኮሪደር ፕሮጀክት በመሠረተ ልማት ለማስተሳሰር በታቀደው መሰረት መተግበሩ መልካም ተሞክሮ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይ የንግድ ትስስር በማቀላጠፍ ለአገር ሁለንተናዊ እድገት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነም አብራርተዋል።
ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችውን የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እንደሚደግፍ ገልጸዋል፡፡
በኬንያ የመንገድ ባለስልጣን ዋና ደይሬክተር ኢንጂነር ዋንጊ ናድሪያንጎ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ይህንን የፈጣን መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ለመከወን ከፍተኛ ድርሻ መጫወታን አመልክተው በኬንያም ከሞያሌ እስከ ላሙ እና ሞምባሳ የሚደርሰው መንገድ ግንባታ የተከናወነ በመሆኑ ወደቦቹ ክፍት መደረጋቸውንም ገልጸዋል።
ይህም ለኢትዮጵያና ለኬንያ የንግድ ማህበረሰቦች እቃዎችን ከወደብ በቀላሉ እንዲያንቀሳቀሱ ለማስቻል የሚረዳ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
የደቡብ ሱዳን መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ቤንጃም ሊቦ፤ ከኢትዮጵያና ኬኒያ የልምድ ልውውጥ በማድረግ ጠቃሚ ነገሮችን እንደሚያገኙና በተለይ የላሙ ወደብና ኮሪደሩን የሚያስተሳስረው ፕሮጀክት ለአገራቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ሚንስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር የሚያስተሳስሩ የመንገድ መሰርተ ልማት ግንባታ በስፋት እያከናወነች ነው።
ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶችን በመገንባት በተለይ በግዙፍ ኢንዱስትሪ እና አግሮፕሮሰሲንግ ፓርኮች ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ጉልህ ሚናን እንደሚጫወት ገልጸዋል፡፡
የአርሶ አደሩን ምርት እና ተጓዥ ዜጎችን የመሰረተ ልማትና የከተማ አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ የወጪ ገቢ ንግዷን የምታቀላጥፍባቸው ኮሪደሮች ላይ ትኩረት ሰጥታ አየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በኩል ቀጣናውን በመንገድ መሰረተ ልማት የማስተሳሰር ስራ በሌሎች ኮሪደሮችም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመው በቅርቡ የተመረቀው የሞጆ መቂ እና መቂ ባቱ መንገዶችን ለትራንስፖርት ክፍት ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ቀሪው እስከ ባቱ ሞጆ ሐዋሳ ያለው መንገድ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በሚቀጥለው አንድ ዓመት ውስጥም ሙሉ ሞጆ ሐዋሳ በፍጥነት መንገድ የሚገናኝ እንደሆነም አብራርተዋል።
የፈጣን መንገድ ፕሮጀክት ግንባታው ከሞጆ መቂ፣ ከመቂ – ዝዋይ፣ ከዝዋይ አርሲ – ነጌሌ፣ ከአርሲ ነጌሌ-ሐዋሳ በአራት ምዕራፍ ተከፍሎ የሚከናወን ሲሆን የአዲስ አበባ – ሞያሌ – ናይሮቢ – ሞምባሳ የመንገድ ኮሪደር አካል ነው።
የኢትዮጵያን የወጪ ገቢ ንግድ እንቅስቃሴን በተሻለ ሁኔታ ለመጠቀም የሚያስች እንደሆነም ታምኖበታል።
የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 13 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን፤ ይህም ከአለም ባንክ፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ከቻይናና ኮርያ ባንኮች በተገኘ ብድር እንዲሁም ቀሪው ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን መሆኑን ኢዜአ ገልጿል።