ሐምሌ 27/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ ለዓለምና ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል የኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስትር አብርሀም በላይ (ዶ/ር) ገለፁ።
ሚኒስትሩ በቻይና አዘጋጅነት በተካሄደው የቻይና-አፍሪካ የሚኒስትሮች የሰላምና የፀጥታ ፎረም ላይ ተሳትፈዋል።
በዚህ ፎረም ላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት ወቅቱ በዓለማችን ሆነ በአካባቢያችን የሚታዩ የፀጥታ ችግሮችን ለመቅረፍ ከሰላም ኃይሎች ጋር በትብብር መስራት የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው ብለዋል፡፡
የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያም በፓን-አፍሪካን መንፈስ አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካዊያን ለመፍታት እንዲቻል በፅናት እየሰራች መሆኗን ገልፀዋል።
የቻይና ሪፐብሊክ መንግሥትም አካታችና ሚዛናዊ አካሄድን በመከተል ለዓለም ሰላምና መረጋጋት እያደረገ ላለው ሚና ያላቸውን ክብርና አድናቆት ተናግረዋል፡፡
“የጋራ ደኅንነትን ለማረጋገጥ አብሮነትና ቅንጅትን ማጠናከር ይገባል” በሚል መርህ በተካሄደው ሁለተኛው የቻይና-አፍሪካ የሚኒስትሮች የሰላምና የፀጥታ ፎረም ከሀምሳ በላይ ሚኒስትሮችና የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች መሳተፋቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW