ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን
(ቴዎድሮስ ኮሬ)
“ሱዳን” የሚለው ቃል “ቢላድ አል-ሱዳን” ወይም “የጥቁሮች ምድር” የሚል ትርጉም ያለው የአረብኛ ቃል ሲሆን፤ የመካከለኛው ዘመን መልክዓ ምድር አጥኚዎች ከሰሃራ ዙሪያ ያለውን አካባቢ ለመጥራት ይገለገሉበት የነበረ ቃል ነው፡፡ በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን፣ “ሱዳን” የኒሎቲክ እና አጎራባች መሬቶች መጠሪያ ሆነ፡፡ መጠሪያ ቃሉ በተከታታይ ቅኝ ገዥዎች እና የ1956ቱን የሀገሪቱን ነፃነት ባቀነባበረው ካርቱም ተኮር ብሄራዊ ንቅናቄ ግልጋሎት ላይ ውሏል። ከዚያ በኋላ በተከሰቱት የእርስ በርስ ጦርነቶች፣ ገና በዕቅድ ላይ ለነበረችውና ላልተመሰረተችው የደቡብ ሱዳን ግዛት የተለያዩ ስሞች ተሰጥተዋል። በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ “ደቡብ ሱዳን” የሚለው ስም እጅግ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቶ ለአሁኗ ደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ስያሜ ሆኗል።
ደቡብ ሱዳን በምስራቅ አፍሪካ የምትገኝ ወደብ አልባ ሀገር ነች። ከረዥም የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ በ2011 ከሱዳን ተገንጥላ ነፃነቷን አግኝታለች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሀገሪቱ እንደ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ የኢኮኖሚ ችግር እና ግጭቶችን የመሳሰሉ በርካታ ፈተናዎች ተጋርጠውባታል። እነዚህ ፈተናዎች ቢኖሩም ደቡብ ሱዳን እንደ ዘይት እና ለእርሻ የሚሆን ለም መሬት የመሳሰሉ ከፍተኛ የተፈጥሮ ሃብቶች አሏት።
አገሪቱ የተመሰረተችው በህዝበ ውሳኔ ሲሆን፣ 99% የሚሆነው ህዝብ ከሱዳን መገንጠልን ደግፎ ነበር። ከሃያ ዓመታት በላይ የዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት በሱዳን መንግስት እና በሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጪ ጦር (SPLA) መካከል ተካሂዷል። ጦርነቱ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ሰዎች ህልፈትና ለበርካቶች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል። የደቡብ ሱዳን ነፃነት፣ ለበርካታ ዓመታት የራሱን ዕድል በራሱ ለመወሰን ሲታገል ለነበረው የደቡብ ሱዳን ሕዝብ እንደ አዲስ ጎህ ታየ።
ደቡብ ሱዳን ከምስረታዋ ጀምሮ በፖለቲካ አለመረጋጋት ስትታመስ ቆይታለች፤ በመንግስት ላይ ተደጋጋሚ ለውጦች እና በርካታ መፈንቅለ መንግስት እና የመፈንቅለ መንግስት ሙከራዎች ተደርገዋል። በግጭቶች ምክንያት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እያሽቆለቆለ ሲሆን፣ የዋጋ ንረት እና የስራ አጥነት መጠን እየጨመረ ነው። ግጭቶቹ ለበርካቶች ህይወታቸውን ማጣትና ከአራት ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት ሆነዋል።
ደቡብ ሱዳን ከሰሃራ በስተደቡብ ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ሶስተኛዋ ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት ያላት ሀገር ናት። ከሞላ ጎደል ሁሉንም የአገሪቱን ወደ ወጪ የሚላኩ ምርቶች የሚሸፍነው ዘይት ነው። የሀገሪቱ ለም መሬት ለግብርና ልማት ተስማሚና ሀገሪቱን ሙሉ ለሙሉ የመመገብ አቅም አለው። የሀገሪቱ የእንስሳት ኢንዱስትሪም ለኢኮኖሚው ትልቅ አስተዋፅዖ ያደርጋል፡፡ ከብቶች በደቡብ ሱዳን ህዝብ ዘንድ የሀብት እና የክብር ምልክቶች ናቸው። የደቡብ ሱዳን የተፈጥሮ ሀብት ለኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት ተመራጭ ነው።
ሳልቫ ኪር ማያርዲት፣ የመጀመሪያው የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ናቸው። የእሳቸው መለያ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ከአናታቸው ላይ የማትለየው ባርኔጣ ናት፡፡ ስቴትሰን የተሰኘችው ይህች ባርኔጣ ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ከነበሩት ጆርጅ ደብልዩ ቡሽ የተበረከተችላቸው ስጦታ ናት።
የደቡብ ሱዳን ጦርነት ሲጀመር የታዋቂዎቹ “ዘ ቢትልስ” ሙዚቃ ተደማጭነት ጣራ ደርሶ ነበር። ደቡብ ሱዳን ለዓመታት በፖለቲካ አለመረጋጋት እና በግጭት ስትታመስ ቆይታለች፤ በዚህም የተነሳ በዜጎቿ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። ኢትዮጵያ እንደ ጎረቤት ሀገር በደቡብ ሱዳን ሰላም እንዲሰፍን ንቁ ተሳትፎ እያደረገች ትገኛለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በደቡብ ሱዳን የአንድ ቀን የሥራ ጉብኝት አድርገው ነበር። ከፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና ከምክትል ፕሬዚዳንት ሬክ ማቻር ጋር ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ ለጎረቤት ደቡብ ሱዳን ሰላምና መረጋጋት ቁርጠኛ መሆኗን ዳግም አረጋግጠዋል።
ሳልቫ ኪር የማቻር ፓርቲ አባልና የማቻር ሚስት የሆኑትን መከላከያ ሚኒስትሯን አንጀሊና ቴኒ ከሳምንታት በፊት ከሥልጣን ማንሳታቸውን ተከትሎ ከማቻር ጋር አዲስ ቅራኔ ውስጥ ገብተዋል። በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የተወሰደው ያልተጠበቀ እርምጃ በሀገሪቱ መረጋጋት ላይ አዲስ ስጋት ፈጥሯል። ተቃዋሚዎች ፕሬዚዳንቱ እርምጃዎቹን እንዲቀይሩ ጠይቀዋል። ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር፣ ኪር ጥያቄውን ካላከበሩ “አማራጮቹ ክፍት ናቸው” ብለዋል።
ኪር በካቢኔው ላይ ለውጦችን ሲያደርግ፣ አብዛኛው ደቡብ ሱዳናውያን በመንግስት ቴሌቪዥን ላይ ከሚነበቡት የሀገሪቱ ርዕሰ መስተዳድር ድንጋጌዎች ውስጥ እንደ አንዱ አድርገው ወስደውት ነበር። ነገር ግን ለኪር የፖለቲካ ተቀናቃኝ እና አሁን ደግሞ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ለሆኑት ሪክ ማቻር፣ የኪር የመከላከያ ሚኒስትር አንጀሊና ቴኒን ማባረር የደቡብ ሱዳንን የእርስ በርስ ጦርነት ያበቃውን የ2018 የሰላም ስምምነት መጣስ ነው።
በአፍሪካ እጅግ ገዳይ እና ረጅም ጊዜ የፈጀው የደቡብ ሱዳን ግጭት የተጀመረው በታህሳስ 2013 ነበር። ይህ የሆነው በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና በቀድሞ ምክትላቸው ሪክ ማቻር መካከል በተፈጠረ የስልጣን ሽኩቻ ነው፡፡ ይህ ግጭት ከመሪዎቹ በፍጥነት ተሻግሮ ወደ ብሄር ግጭት ተሸጋገረ፡፡ በዚህም የኪር ጎሳ በሆኑት ዲንቃዎች እና የማቻር ጎሳ በሆኑት ኑዌሮች መካከል ጦርነት ተቀሰቀሰ። ጦርነቱ ከ400 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፣ ሚሊዮኖችን አፈናቅሏል፣ በአካባቢው ላይ ሰብአዊ ቀውስ አስከትሏል።
በተፋላሚ ወገኖች መካከል በርካታ የሰላም ስምምነቶች ተፈራርመዋል፣ ነገር ግን አንዳቸውም በበቂ መልኩ ሊፈፀሙ አልቻሉም። በመስከረም 2018 የተፈረመው የቅርብ ጊዜው የሰላም ስምምነት አሁንም ፈተናዎች እያጋጠሙት ነው፣ አፈጻጸሙም አዝጋሚ ሆኖ ሰንብቷል።
ግጭቱ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ትኩረትን ስቧል። ግጭቱን በማስታረቅ ረገድ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች። ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ጎረቤት በመሆኗ ከግጭቱ ተጽዕኖ ማምለጥ አትችልም፤ በሺዎች የሚቆጠሩ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ መሰደዳቸው ለዚህ አባባል አንድ ማሳያ ነው። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሁለቱን ወገኞች ለማስታረቅ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተው፣ በመጨረሻም ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ በተፋላሚ ወገኖች መካከል የመስከረም 2018 የሰላም ስምምነት ተደርጓል። ይሁን እንጂ የስምምነቱ አፈጻጸም ፈተና እንደሆነ ቀጥሏል።
ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ግጭት ውስጥ ያላትን ተሳትፎ ለመረዳት ታሪካዊ ግንኙነታቸውን መፈተሽ አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ካገኘች 2011 ጀምሮ በሀገሪቷ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ቁልፍ ሚና በመጫወት ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ነፃ እንድትወጣ በተደረገው ድርድር ላይም ትልቅ ድርሻ ነበራት።
ይሁን እንጂ፣ በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና በቀድሞ ምክትላቸው በሪክ ማቻር መካከል በተፈጠረ የስልጣን ሽኩቻ ምክንያት ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ካገኘች ከሁለት ዓመታት በኋላ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ገባች፡፡ ኢትዮጵያ ጦርነቱ መቋጫ እንዲያገኝና ሰላም እንዲሰፍን ብዙ ጥረት አድርጋለች፡፡ በተፋላሚ ወገኖች መካከል የተደረጉ በርካታ ዙር የሰላም ድርድሮችን አካሂዳለች።
ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን የምታደርገው ጥረት ለቀጣናው መረጋጋት ባላት ቁርጠኝነት ላይ ብቻ ሳይሆን ለራሷም የውስጥ ደህንነት ስጋት በመሆኑ ጭምር ነው። ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር የምትዋሰን ሲሆን በደቡብ ሱዳን ግጭት ሳቢያ በስደተኞች ፍሰት እና በድንበር ዘለል የጸጥታ እጦት ስትጎዳ ቆይታለች።
ምንም እንኳን የተለያዩ እንቅፋቶች ቢያጋጥሟትም፣ ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን የምታደርገው ተሳትፎ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል። ለሰላም ድርድር እና ሽምግልና የምታደርገው ያላሰለሰ ጥረት ለግጭቱ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ያላትን ጽኑ ፍላጎት ያንጸባርቃል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ተሰሚነት ያላት በመሆኑ ዲፕሎማሲያዊ ተጽዕኖዋን ተጠቅማ ተፋላሚ ወገኖችን ወደ ድርድር ጠረጴዛ በተደጋጋሚ አምጥታለች። በገለልተኛ መንገድ በሱዳን መንግስት እና በተቃዋሚዎች መካከል ያለውን የሰላም ድርድር እንዲካሄድ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥራለች።
በ2018 በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና በአማፂው መሪ ሪክ ማቻር መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት በማድረግ ረገድ ኢትዮጵያ ትልቅ ሚና ተጫውታለች። ይህ ስምምነት በኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ የተፈረመ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አሸማጋይነት የተካሄደ ነበር።
ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን የሰላም ሂደት ያስመዘገበችው ስኬት፤ ሀገሪቱ ከመንግስትም ሆነ ከተቃዋሚዎች ጋር ባላት ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ የተመሠረተ ነው። በድርድሩ ላይ ያሳየችው ገለልተኝትም በሁሉም አካላት አመኔታ እንድታገኝ አድርጓታል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም ፈጣሪ የመሆን ታሪክ አላት። ኢትዮጵያ ከሶማሊያ፣ ከሱዳን እና ከኤርትራ ጋር በጋራ ግጭቶችን በመፍታትና ለእርቅና ሰላም በመስራት በኩል ቁልፍ ሚና ተጫውታለች። ይህም ልምዷ በደቡብ ሱዳን በግጭት አፈታትና የሰላም ሂደት ውስጥ ወሳኝ ድርሻ እንዲኖራት አድርጓታል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ድርድርን በማመቻቸት፣ በግጭቱ ለተጎዱ ሰብዓዊ ዕርዳታ በመስጠትና የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በመደገፍ ተሳትፎ አድርጓል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ የተለያዩ የእርዳታ ፓኬጆችን በመያዝ የሀገሪቱን መሠረተ ልማቶች እና ተቋማትን መልሶ በመገንባት ሂደት ድጋፍ በማድረግ በኩል ወሳኝ ሚና እየተጫወተች ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት በደቡብ ሱዳን ወገኖች መካከል ሰላም እንዲሰፍን በንቃት መሳተፉ ብቻ ሳይሆን፣ በግጭቱ ሳቢያ ለተፈናቀሉ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የመጠለያ ስፍራ ሰጥቷል። ውጥረቱን ለማርገብ እና በግጭቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመጠበቅ፣ የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ ጥያቄ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ልኳል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ጦር ለደቡብ ሱዳን ጦር ኃይል በክህሎትና እውቀት አቅም ግንባታ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ውስጥ በተለያዩ ቡድኖች መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ የሚረዳ በጣም ወሳኝ የገንዘብ እና የግብአት ድጋፍ አድርጋለች። ይህም ተፋላሚ ጎሳዎች በሰላማዊ መፍትሔዎች ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት በማሻሻል ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው።
ኢትዮጵያ ባደረገችው ተሳትፎ ሁሉም ወገኖች በአንድነት በመሰባሰብ የእያንዳንዱን ወገን ፍላጎትና ጥቅም የሚፈታ ዘላቂ የሰላም ስምምነቶች መፍጠር ችለዋል። ይህም ለደቡብ ሱዳን መረጋጋት እና አንድነት መንገድ ይጠርጋል።
ኢትዮጵያ በሰላም ድርድር ጠረጴዛው ብዙ ጥቅሞችን ብታስገኝም እንኳን፣ አሁንም መታለፍ ያለባቸው በርካታ ፈተናዎች አሉ። በደቡብ ሱዳን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ በጣም ተለዋዋጭ ነው፡፡ ትንሽ የሚባሉ የአመራር ለውጦች እንኳን የሰላም ሂደቱን ሊያደናቅፉ ይችላሉ። ይህም በኢትዮጵያ ተሳትፎ ላይ ችግር ይፈጥራል፡፡ ስለሆነም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አሸማጋዮች በመሬት ላይ ያሉትን ለውጦችን ተንተርሰው ያለማቋረጥ ስልቶቻቸውን እንደ አዲስ ማስተካከል ይኖርቸባዋል።
በደቡብ ሱዳን ውስጥ ያሉት ሁለቱ ዋና ዋና ተፋላሚ ወገኖች በቁልፍ ጉዳዮች ላይ በጣም የተለያየ አቋም ስላላቸው፣ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ገለልተኛ አካል በመካከላቸው መግባባት ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት አስቸጋሪ ያደርግበታል።
ኢትዮጵያ በተፋላሚ ወገኖች መካከል የሚደረገውን ድርድር በማመቻቸት ረገድ የሃብት ውስንነት አለባት። ይህም በኢትዮጵያ በኩል ውጤታማ ሽምግልና ለማድረግ፣ የተደረጉ ስምምነቶችን ወይም ሌሎች የሁለቱም ወገኖች እርምጃዎችን ለማስፈጸም እንቅፋት ይሆናል። በቂ ግብአት ከሌለ አሸማጋዮች ሽምግልናውን ሳይቆራረጥና ሂደቱን ጠብቆ ግጭቱን ለመፍታት በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ችግር ይገጥማቸዋል። ኢትዮጵያ፣ እነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ቢያጋጥሟትም በደቡብ ሱዳን ያለውን ግጭት በመፍታት ሂደት ውስጥ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ማድረግ እንደምትችል አስመስክራለች።
የደቡብ ሱዳን ህዝብ ትልቅ ስራ ይጠብቀዋል። ኢትዮጵያ የሚፈልጉትን ሰላም ለማምጣት የተሻለ ዕድል እንዲኖራቸው እየረዳች ነው። ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ዘላቂና ትርጉም ያለው ሰላም ለማምጣት የምታደርገውን ጥረት በመደገፍ በኩል ሁሉም ሃገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት የበኩላቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች በሰላም ድርድሩ ውጤታማ ሆናለች፡፡ በአንድ በኩል ለድርድር ምቹ ሁኔታና ቦታ ፈጥራለች። ይህ ለሁለቱም የግጭት አካላት መገልገያዎችን መስጠት እና በገለልተኛ ሁኔታ ውስጥ ግልጽ ውይይት ማድረግን ያካትታል፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ መፍትሄዎች ትኩረት ሰጥታለች። ይህም ሁለቱም የግጭት አካባቢዎች እንደገና እንዲገነቡና ሰላማዊ የወደፊት ጉዞ እንዲደረግ የሚያግዙ ፕሮጀክቶችን ያካትታል።
የኢትዮጵያ መንግስት ጥረት ትኩረት ሳይሰጠው ሊታለፍ የሚችል አይደለም። የደቡብ ሱዳን ህዝብ ኢትዮጵያ በሰላማዊ ድርድር ላይ ላደረገችው ንቁ ተሳትፎ ታላቅ ምስጋና አቅርቧል። ከዚህ በተጨማሪም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ባደረገችው አስተዋፅዖ እና በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ለተጫወተችው ሚና አድናቆቱን ቸሯታል።
ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን የሰላም ሂደት በዋጋ የማይተመን አስተዋጻዖ እንደነበራት የሚታወቅ ነው። ኢትዮጵያ ለግጭቱ ዘላቂ እና ትርጉም ያለው መፍትሄ ለማግኘት ያላትን ቁርጠኝነት በድርድሩ ንቁ ተሳታፊ በመሆን አሳይታለች። አበረታች ውጤቶችም አስመዝግባለች፡፡ በመሆኑም ለደቡብ ሱዳን ግጭት ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ለሰላም ሂደቱ አጋዥ የሆኑ መሳሪያ እና ግብአት ለኢትዮጵያ የማሟላት ጉዳይ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ነው። የኢትዮጵያ ቁርጠኝነት እና እውቀት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ጋር ተደምሮ በደቡብ ሱዳን ሰላምን ለማስፈን የሚያስችል አመርቂ ስራዎችን መስራት ይቻላል።
የደቡብ ሱዳን መሪዎችም ሀገሪቱ ያላትን አቅም እውን ለማድረግ በሀገሪቱ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን መስራት አለባቸው። አለም አቀፉ ማህበረሰብም ደቡብ ሱዳን ለሰላም፣ መረጋጋት እና ልማት የምታደርገውን ጥረት አጠናክሮ መደገፍ አለበት።