ኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ የምታደርገው ጥረት ይደነቃል – ፕሬዝዳንት ሳልቫ

ነሃሴ 20/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ የምታደርገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት ገለጹ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የውጭ ቋንቋዎችና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት ከጠቅላይ ሚኒስት ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በሁለትዮሽና በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።

ውይይታቸው በአገራቱ መካከል ያለውን ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች በተለይም የመሰረተ-ልማት ትስስር ሊጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

በውይይቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ መስጠታቸውንም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የተለያዩ ችግሮች ቢገጥሟትም በዋና ዋና አኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ አዎንታዊ ለውጦች ማስመዝገብ መቻሏን ለፕሬዝደንቱ አብራርተውላቸዋል።

በአገሪቱ ያለውን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት በተመለከተ አስረድተዋቸዋል።

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት በበኩላቸው ኢትዮጵያ ስኬታማ ምርጫ ማድረጓን አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንኳን ደስ አለዎት ብለዋቸዋል።

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት ማጠናቀቅ መቻሏንም አድንቀዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በማድረስ ግጭት መቀስቀሱን በጽኑ ማመውገዛቸውን ቢልለኔ ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርቱን ለመጠበቅ የሚያደርገውን ጥረት በአድናቆት እንደሚመከቱት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ላጋጠማት የውስጥ ችግር የውጭ ጣልቃ ገብነት እንደማያስፈልግም ፕሬዝዳንቱ ማንሳታቸውን ተጠቁሟል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጠውም ፕሬዝዳንቱ መግለጻቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገልጿል።